
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢቲዮ-ቴሌኮም በወቅቱ የክፍያ መጠየቂያ (ቢል) ባለማቅረቡ የዕዳ ክምችት እንዳለባቸው የግምጃ ቤት ከተማ ነዋሪዎች እና የመንግሥት ተቋማት ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የተቋሙ የአገልግሎት አሠጣጥ ችግረም የቅሬታቸው ምንጭ ሆኗል፡፡
የከተማው ነዋሪዋ ወይዘሮ አንጀት አምሳል የቤት ስልክ ተጠቃሚ ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙት በቴሌኮሙ ማዕከል አማካኝነት መረጃ ሲደርሳቸው ነበር፤ ነገር ግን ሦስት እና አራት ወራትን ዘግይቶ ይደርሳቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ 2012 ዓ.ም ከገባ ጊዜ ጀምሮ ምንም ክፍያ አለመፈጸማቸው ከፍተኛ የዕዳ ክምችት እንዳይኖርባቸው ስጋት አሳድሮባቸዋል፡፡
የመንግሥት ተቋማትም የችግሩ ሰለባ መሆናውን የወረዳውን ስፖርት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች እና ግብርና ጽሕፈት ቤቶችን አነጋግረን ማረጋገጥ ችለናል፡፡ ተቋሙ አስቀድሞ የክፍያ መጠን አሳውቆ ቢል ሳያቀርብ ‘ክፍያ አልተፈጸመም’ በማለት አገልግሎት የተቋረጠበት ጊዜ መኖሩንም የስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ካሳሁን ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የወረዳው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታማኙ ዮሐንስ እንዳሉት ኢቲዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አለበት፡፡ የመንግሥት ተቋማት በተደጋጋሚ ቅሬታ እና ክስ ውስጥ ይገባሉ፤ ግለሰቦችም አገልግሎቱን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡ የመንግሥት ተቋማት በወቅቱ ክፍያ አለመፈጸማቸው ደግሞ በፋይናንስ አስተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓታቸው ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ችግሩ በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚኖር በማመላከት ‘‘መፍትሔ እንዲኖረው ይሠራል’’ ብሏል፡፡ የችግሩ ምክንያት የተቋሙን አሠራር ለማዘመን በሚወሰዱ የመሻሻያዎች አለመግባባት መፈጠሩን በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኦትሬሽን ዳይሬክተር ጀምበር ታደለ አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ብሎ የክፍያ ቢል ይቀርብ የነበረው በአቅራቢያ በሚገኝ የሽያጭ ማዕከልና የሽያጭ ማዕከል በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በሕዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማኅበር በኩል እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል፡፡
የከፍያ ማሳወቂያ (ቢል) ሕትመት አወዋጪ ባለመሆኑ ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ የቴለክኖሎጂ አማራጮችን ተጠቅሞ ማስከፈል ጀምሯል፡፡ እየተጠቀመ ያለውም በባንክ መክፈል፣ ይሙሉ ወይንም መደበኛ ካርድን ተጠቅሞ የአየር ሰዓት መሙላት እና የ ሲ ኢ ብር የክፍያ አማራጮችን ነው፡፡ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ክፍያ ያልፈጸሙ የመንግሥት ተቋማት እና ደንበኞች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ችግር ክፍያ አልፈጸማችሁም በሚል የአገልግሎት መቋረጥ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል በተቻለ ፍጥነት ወደ መፍትሔ ይገባል ብለዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ተዘዋውሮ ቅስቀሳ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ግንዛቤ መፍጠሪያ አማራጮችን እንደሚጠቀምም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
