
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በባሕር ዳር ከተማ ሀገረ ሰላም ቀበሌ አቅመ ደካማ፣በሕመም የሚሰቃዩ እና አካል ጉዳተኛ የኾኑ ቤተሰቦችን ቤት የማደስ ሥራ አስጀምሯል።
ወይዘሮ ስለናት ፈንቴ እና ባለቤታቸው አቶ ምሥጋናው ክንዱ በባሕር ዳር ከተማ ሀገረ ሰላም ቀበሌ ነዋሪዎች ሲኾኑ ሦስት ልጆችንም ወልደዋል።
ወይዘሮ ስለናት ፈንቴ እንዳሉት ሦስቱም ልጆቻቸው አካል ጉዳተኞች በመኾናቸው እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው የቀን ሥራ መሥራት አልቻሉም።
በመኾኑም የአካባቢው ማኅበረሰብ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ሕይዎታቸውን እየገፉ ይገኛሉ።
ከኑሮ ጫናው ባለፈም ክረምት በመጣ ቁጥር ያዘመመ፣ ጣራው የተቀዳደደ እና ግድግዳው የወላለቀ ቤታቸው እያፈሰሰ እና ጎርፍ እያስገባ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የነርቭ ሕመምተኛ በመኾናቸው ለመንቀሳቀስ የተቸገሩት አቶ ምሥጋናው ክንዱ “ዛሬ የወደቀው ቤት በአዲስ ለመገንባት ሥራው በመጀመሩ ተደስቻለሁ” ነው ያሉት።
የክረምቱን መግባት ተከትሎም የቀበሌው መሪዎች ቤታቸውን ለመሥራት እቅድ መያዙን አስቀድሞ ሲነግሯቸው ያላመኑት ወይዘሮ ስለናት እና አቶ ምሥጋናው ዛሬ ቃል በተግባር ሲፈጸም በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በሀገረ ሰላም ቀበሌ ነዋሪ የኾነው ወጣት ጸጋዬ ድረስ “ዝናብ፣ ጎርፍ እና ብርድ እየተፈራረቀ የሚቸገሩትን አቅመ ደካማ ግለሰቦች ቤት ሥራ ሲጀመር ተሳታፊ በመኾኔ ተደስቻለሁ” ነው ያለው። ወደፊትም በመሰል የበጎ አድራት ሥራዎች ተሳታፊ እንደሚኾንም ተናግሯል።
በበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የማኅበራዊ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ብርቱካን ሞላ የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናቆ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የአቅመ ደካሞችን ቤት በአዲስ መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን፣ ባለሀብቶችን እና ተቋማትን የገንዘብ ብሎም የጉልበት ድጋፍ በመጠየቅ የበርካታ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመጠገን ወይም በአዲስ ለመሥራት መታቀዱንም ወይዘሮ ብርቱካን ጨምረው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ድጋፍ ዛሬ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመሥራት መርሐ ግብር በሀገረ ሰላም ቀበሌ መጀመሩን ነው ኀላፊዋ የተናገሩት። ሌሎች ተቋማትም የኢንስቲትዩቱን ፈለግ እንዲከተሉ አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሥራቴ ሙጨ “ይህ የአቅመ ደካማ ግለሰቦችን ቤት የመሥራት ተግባር የዘንድሮው የክረምት በጎ አድራጎት ሥራ አንዱ አካል ነው” ብለዋል። ሌሎች መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ ባለሀብቶች እና ግለሰቦችም መሰል የበጎ አድራጎት ሥራ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሠለ የማኅበረሰብ አገልግሎትን የማከናዎን ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት። በመኾኑም በየዓመቱ ኢንስቲትዩቱ የበጎ አድራጎት ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
በበጎ አድራጎት ተግባር መሳተፍ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን እና አብሮ የመሥራት በጎ ምግባር በመኾኑ 240 ሺህ ብር በጀት በመመደብ የአቅመ ደካማ ግለሰቦችን ቤት መገንባት አስጀምረናል ነው ያሉት።
ይህን ሰው ተኮር የማኀበረሰብ አገልግሎት በስፋት እና በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን