
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናዎች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የዋና ጠቅላይ መምሪያው ምክትል አዛዥ እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በሰጡት መግለጫ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ለዚህም ተፈታኞች፣ አስፈታኞ፣ የጸጥታ መዋቅሩ እና መላው ሕዝብ ቀና ትብብር ማድረጉን ገልጸዋል።
የመልስ መስጫ ወረቀቶችም ወደ ማዕከል እየተሰባሰቡ መኾኑን ገልጸዋል። በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 04/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም በሰላም መጠናቀቁን በመግለጫቸው አንስተዋል። ለዚህም የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ እና የጸጥታ ኀይሉን አመስግነዋል።
በክልሉ የተከናወኑ ተግባራት በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የጸጥታ መዋቅሩን እና መላውን ሕዝብ አመስግነዋል። የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከፌደራል የጸጥታ መዋቅር ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት እና አንጻራዊ ሰላሙን በመፍጠር ውጤት የተመዘገበበት መኾኑንም አንስተዋል። ምስጋናቸውንም ገልጸዋል።
የተማሪዎች ፈተና በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ በመተባበሩ ያለ ምንም ችግር መጠናቀቁንም ነው ምክትል ኮሚሽነር አበበ የጠቀሱት። ሕዝቡ የሰላም ፍላጎቱን በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ላይ መግለጹን ጠቅሰው ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ባሕር ዳር በመምጣት የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶችም ይህንኑ የሰላም ፍላጎት ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
ሁለቱም ክልላዊ ክዋኔዎች በሰላም እንዲፈጸሙ የጸጥታ መዋቅሩ አቅዶ፣ ተወያይቶ፣ የሥራ ክፍፍል አድርጎ እና ተቀናጅቶ በመሥራቱ ክልላዊ ተግባራቶቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ማስቻሉን ነው የገለጹት።
የክልሉ ሕዝብ እና የጸጥታ መዋቅሩ በቀጣይ የመማር ማስተማሩን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች በሰላም እንዲቀጥሉ እና እንዲሰፉ መሥራትን እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን