ከተሞችን በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለማስተሳሰር የሚያስችል ድጋፍ ተደረገ።

11

አዲስ አበባ: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ የ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ክልላዊ የመልማት ጥናት ርክክብ መደረጉን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የዘጠኝ ከተሞችን ክልላዊ የመልማት ጥናት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ሀቢታት ድርጅት ተረክቧል።

ጥናቱን የተረከቡት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታው ፈንታ ደጀን በሀገር እና በክልል ደረጃ ከተሞችን የሚያገናኝ የመልማት ጥናት ተግባራዊ ባለመደረጉ በከተሞች ያለውን ጸጋ ለይቶ በአግባቡ ለመጠቀም እና የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ለማጠናከር ክፍተት እንደነበር አንስተዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የተሠራው ክልላዊ የመልማት ጥናት የሀገሪቱን ከተሞች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለማስተሳሰር እና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል። ጥናቱ በሀገሪቱ ባሉ የክልል ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ነው ብለዋል።

ጥናቱ የኢትዮጵያን ከተሞች ከአጎራባች ሀገራት ከተሞች ጋር ያለውን ማኅበራዊ ትሥሥር እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል መኾኑንም ሚኒስትር ድኤታው አንስተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪነት የተሠራው የክልሎች የመልማት ጥናት የክልሎችን የመልማት እምቅ አቅም ለማሳደግ እና የጎላ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ሀቢታት ዳይሬክተር ሚስተር ኢሻኩና ናቸው።

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኾነው ዩኤን ሀቢታት ረጅም ግንኙነት ያላቸው መኾኑን የጠቀሱት ሚስተር ኢሻኩና ይህ ከግንኙነቶች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል። ጥናቱ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሲኾን በተለይም የክልል ከተሞችን ውሕደት የሚያበረታታ እንደኾነ ነው የገለጹት።

በሀገሪቱ ያሉት እያንዳንዳቸው ክልሎች የራሳቸው የኾነ ጥንካሬ እና አቅም ያላቸው ሲኾን ጥናቱም የእያንዳንዱን ክልል እምቅ አቅም ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል። ክልሎች ከክልሎች ጋር ያላቸውን ሁለንተናዊ የተቀናጀ የልማት እድገት በማጠናከር ረገድም ጠቀሜታው ከፍ ያለ መኾኑን አንስተዋል።

ዩኤን ሀቢታት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመሪዎች የሕዝብን አደራ ተቀብለው በመሥራት የዘመኑ የልማት አርበኛ መኾን እንደሚገባቸው የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየተማሪዎች ክልላዊ ፈተና እና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ፡፡