
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በ2006 ዓ.ም ሥርጭቱን የጀመረው አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተለያዩ ሚዲዬሞች ሕዝቡን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ሥራውን በበኩር ጋዜጣ በ1987 ዓ.ም የጀመረው አብመድ በ1989 ዓ.ም አማራ ራዲዮን፣ በ1992 አማራ ቴሌቪዥንን፣ በ1994 ደግሞ አማራ ባሕር ዳር ኤፍ ኤም 96.9 ጣቢያዎቹን ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮም በአዲሱ ሚዲያ (ኦንላይን ሚዲያ) ዓለማቀፍ ተከታታዮችን ጭምር እያገለገለ ይገኛል፡፡
በ2006 ዓ.ም ደግሞ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ላይ ሁለት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችን ሥራ አስጀምሯል፡፡ በወቅቱ ደሴ ኤፍ ኤም 87.9 እና ደብረ ብርሃን ኤፍ ኤም 91.4 ተብለው ይጠሩ የነበሩት ጣቢያዎችም ሥርጭታቸውን ግንቦት 19 እና 20/2006 ዓ.ም ነበር የጀመሩት፡፡
የኤፍ ኤም ጣቢያዎቹን እያሰፋ የሚገኘው አብመድ ሥያሜያቸው ወጥነት እንደኖረው ለማድረግ መነሻቸው ላይ የጋራ መጠሪያ በማስቀደምና የሚገኙበትን ከተሞች ሥም በማስቀጠል ሰይሟል፡፡ ስያሜዎቹን ለማሻሻልም በኦንላይና በጽሑፍ መጠይቅ ሐሳብ ከአንባቢዎችና አድማጮች መቀበሉ ይታወሳል፡፡
አማራ ኤፍ ኤም ደሴ 87.9 ሥርጭቱን የጀመረበትን ስድስተኛ ዓመት ዛሬ እያከበረ ነው የሚገኘው፡፡ ጣቢያው አካባቢያዊ ሽፋኑን ጨምሮ ለ24 ሰዓታት እያገለገለ ይገኛል፡፡
ከራዲዮ ሥርጭት በተጨማሪም የአካባቢውን የዘገባ ሽፋን ለማሳደግ የቴሌቪዥን ዘጋቢዎችን በቋሚነት መድቦ እያሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም ለወሎ እና አካባቢው ኅብረተሰብ ድምጽ እየሆነ ይገኛል፡፡
የጣቢያው ኃላፊ እና የዜና እና ፕሮግራም ምክትል ዋና አዘጋጅ አብዱ ሙሐመድ ጣቢያው ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ጥያቄዎች እና ሐሳቦች በነፃነት እንዲገልጽ ዕድል መስጠቱን በመግለጽ ሥርጭቱን በጥራትና በሽፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ደሴ ላይ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ ለመገንባት የተለያዩ ተግባራትን እየተከናወኑ መሆኑንም ጣቢያ ኃላፊው አስታውቋል፡፡
አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ላይ ያስገነባቸው ኤፍ ኤም ጣቢዎችም አማራ ኤፍ ኤም ጎንደር 105.1 እና አማራ ኤፍ ኤም ደብረ ማርቆስ 95.1 በሚል ሥያሜ በሙከራ ሥርጭት ላይ ይገኛሉ፡፡
ድርጅቱ በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ አዊኛ፣ ኽምጠኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ሥርጭቱን ለሕዝብ እያደረሰም ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዋር አባቢ -ከደሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
