
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ዙሪያ ከሰኔ 06/2017 ዓ.ም እስከ 13/2017 ዓ.ም ለክልሉ መሪዎች የሚሰጠው ሥልጠና ተጀምሯል። ሥልጠናው “አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰጥ ሲኾን የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተሳታፊዎች ናቸው።
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል። ሥልጠናው የተዘጋጀው ከአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ነው። በሥልጠናው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) የሀገር እና ሕዝብ ዕድገት እና ልማት መጨረሻ የሌላቸው የትውልዶች ቅብብሎሽ እና የጥረት ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
የረጅም ጊዜ የልማት ዕቅድ በትውልዶች መካከል የሚደረግ የማኅበረሰብ ዕድገት እና ልማት እንዳይቋረጥ የሚያስችል ዋነኛ ድልድይ ስለመኾኑም አንስተዋል። ለአንድ ሀገር የዕድገት አቅሞች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የተፈጥሮ ሃብትን መሠረት ያደረገ ካፒታል፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚኾን ቁሳዊ ካፒታል፣ ሰብዓዊ ካፒታል፣ ማኅበራዊ ካፒታል እና ቴክኖሎጅ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። እነዚህን አቅሞች በአግባቡ እና በዕቅድ እየመሩ መጠቀም ደግሞ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ስለመኾኑ አመላክተዋል።
በግጭት አዙሪት ምክንያት እነዚህ አቅሞች ለአሻጋሪ ዕድገት መነሻነት በማይበቁበት ደረጃ ኾነው መቆየታቸውንም አመላክተዋል። የተዛቡ ትርክቶች መበራከታቸው እና ቴክኖሎጂ እና ሳይንስን እንደችግር መፍቻነት አለመጠቀም ለችግር እና ለድህነት እንደሚዳርግም ጠቅሰዋል።
እንደ አማራ ክልልም ያሉትን የዕድገት አቅሞች አሟጦ መጠቀም ባለመቻሉ 26 ነጥብ 1 በመቶው የክልሉ ነዋሪዎች ዛሬም በድህነት ውስጥ እየኖሩ ነው ብለዋል። ለዘመናት በተነዛው ስሁት ትርክት ምክንያት የሚነሳው ግጭት የማኅበራዊ ካፒታል መሸርሸርን እያስከተለ ስለመኾኑ አመላክተዋል።
በክልሉ የሚስተዋለውን የግጭት አዙሪት በመፍታት የሕዝቡን ሰላም እና ብልጽግና ለማረጋገጥ በዕቅድ መመራት እጅግ ወሳኝ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የአጭር እና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን በአግባቡ አስተሳስሮ ማዘጋጀት፤ በጋራ እና በትጋትም መፈጸም ለነገ የማይባል ወሳኝ ጉዳይ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች በሙሉ ዓቅሙ ልማት ላይ እንዳያተኩር ተግዳሮት ገጥመውት እንደቆዩ አብራርተዋል። ይኹን እንጅ ልማት ከችግር መውጫ ብቸኛው መንገድ መኾኑን ተገንዝቦ እየሠራ ነው ብለዋል።
የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች፣ ሀገር ወዳድ ምሁራን እና የዘርፉን ባለሙያዎች ሁሉ በማስተባበር የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ እና በመሥተዳድር ምክር ቤቱ አጽድቆ በ2018 በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል። ይህ ዕቅድ በዋነኛነት በክልሉ የገጠመውን የግጭት እና የድህነት አዙሪት ፈጥኖ ለመስበር መፍትሄ ያስቀመጠ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ዕቅዱ ሦስት ደረጃዎችን ማለትም የኢኮኖሚ መረጋጋት እና ማገገም ፕሮግራም፣ የመመንጠቅ ደረጃ እና የመበልጸግ ደረጃን የያዘ ስለመኾኑም ተንትነዋል። ዕቅዱ ከሀገር አቀፍ የረጅም ዘመን ርዕይ እና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ዕቅድ ጋር ተናባቢ ኾኖ የተዘጋጀ ሲኾን ባለቤቱም ሕዝቡ ነው ብለዋል።
“የልማት ዕቅድ የሕዝብ ነው፤ የሚተገብረው እና በውጤቱ የሚጠቀመውም ሕዝቡ ነው” ብለዋል። ሕዝብ ያለመሪዎቹ አስተባባሪነት በተደራጀ መንገድ በልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ ስለሚቸግረው መሪዎች የሕዝብን አደራ ተቀብለው በመሥራት የዘመኑ አርበኛ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት። በየደረጃው የሚገኙ ፈጻሚዎችን ለማብቃት እና የሚመሯቸው ተቋማትም ምስጉን አገልጋይ እንዲኾኑ ለማስቻል ሥልጠና ስለመዘጋጀቱም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን