“የሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል አሻጋሪ እቅድ አዘጋጅቶ መሥራት ምርጫ ሳይኾን ግዴታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

39

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ዙሪያ ከሰኔ 06 እስከ 13/2017 ዓ.ም ለክልሉ መሪዎች የሚሰጠው ሥልጠና ተጀምሯል። ሥልጠናው “አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የሚሰጥ ሲኾን የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተሳታፊዎች ናቸው።

በሥልጠናው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ክልል በክልል ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ዛሬ የጀመረው የከፍተኛ መሪዎች ሥልጠናም የፍኖተ ካርታውን ጉዞ ለማስጀመር እና በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሚተገበሩ ሥራዎች ላይም የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያስችል ነው ብለዋል። ሥልጠናው ትልቅ የመልማት ጸጋ ያለውን ክልሉን መሠረት በማድረግ የወደ ፊት የጋራ ርዕያችንን እና መዳረሻችንን የምንበይንበት መድረክ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሥልጠና መድረኩ ከውይይት እና ንግግር በተጨማሪ በተግባርም የክልሉን ሕዝብ ከግጭት እና ከድህነት አዙሪት በማላቀቅ ከሚፈለገው ከፍታ ላይ ለማስቀመጥ ቃል ኪዳን የምናስርበት መድረክ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ግጭት እና ድህነት እየተመጋገቡ እና እየተፈራረቁ የሕዝባችን ችግር ኾነው ቆይተዋል፤ ይህ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ በጋራ አመራር በትጋት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ሕዝባችን የደህንነት፣ የአብሮነት፣ የማደግ እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላትም አልፎ ዓለም የደረሰበትን ቅንጡ አኗኗር መኖር ያሻል፤ ከሕዝብ ፊት ያለን መሪዎች ይህንን የሕዝብ ፍላጎት በውል በመረዳት መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

ለሕዝባችን መልማት እና ለክልሉ አንድነት ቀናዒ ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር ሁሉ በመመካከር የ25 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ተነድፏል፤ በዚህ ፍኖተ ካርታ አተገባበር ላይ በጥልቀት ውይይት ይደረጋል፤ የግለሰብ ሳይኾን የብዙኅን አንሰላሳይነትን ባቀፈ ሃሳብ ላይ በመመስረትም የወደ ፊት የጋራ መዳረሻችንን እንተልማለንም ብለዋል።

እንደ መሪ በአጭር እና በረጅም ጊዜ እቅዶቻችን እንዲሁም በተቋማዊ እና ክልላዊ ግቦቻችን የጋራ ርዕይ እና ፍላጎትን አጠንክሮ መያዝ ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል። አንድነት እና ግልጸኝነት ተባዥ ውጤት ያለው የሥኬት ምንጭ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የሥልጠና መድረኩ የታቀዱ እቅዶችን በተከታታይነት፣ በዘላቂነት እና በተደማሪነት ለመተግበር የጋራ ቃልኪዳን የሚታሰርበት ሥለመኾኑም ተናግረዋል።

“ከዶሮ ብታልም… ዓይነት እቅድ እንውጣ” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ሕዝብ ከግጭት መላቀቅ እና መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ብቻ ሳይኾን ቅንጡ ኑሮ መምራትም እንደሚፈልግ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። መሪዎች ተስፋ ያለው እና የይቻላል መንፈስን የተላበሰ ሕዝብ የመቅረጽ ኀላፊነት አለባቸው፤ መሪዎች ፊት ላይ ኾነው ሕዝብን በውጤታማነት በመምራት ተጨባጭ ለውጥም ማምጣትም ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የሀገራቸውን ውስብስብ ችግር ፈትተው የሚመሩትን ሕዝብ በከፍታ ላይ ያስቀመጡ የሀገራት መሪዎች ሁሉ ስማቸው በከፍታ ላይ ተቀምጦ እናገኘዋለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝባችን የገጠመውን ችግር መፍታት እና ኅብረተሰቡን በከፍታ ላይ ማስቀመጥ፣ መሪዎችም ስማቸውን በበጎ ታሪክ ላይ ማጻፍ አለባቸው ነው ያሉት።

ሕዝቡ በተስተካከለ ሕይዎት እና በተሻሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲደርስ መሪዎች መስዋዕትነት ጭምር እየከፈሉ መሥራትን ባሕል ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። ጠንካራ የኾነ የተቋማት እና የሥራ አመራር ባሕልን በመላበስ ሕዝብን ማገልገል ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በግጭት እና በድህነት አዙሪት ውስጥ መቆየት የማንም ምርጫ ሊኾን አይችልም፤ በመኾኑም የሕዝብን ደህንነት እና የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል አሻጋሪ እቅድ አውጥቶ በጋራ መሥራት ምርጫ ሳይኾን ግዴታ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከ242 ተሳፋሪዎች አንዲት ነፍስ ብቻ የተረፈችበት የኤር ሕንድ የአውሮፕላን አደጋ።
Next articleመሪዎች የሕዝብን አደራ ተቀብለው በመሥራት የዘመኑ የልማት አርበኛ መኾን እንደሚገባቸው የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አስታወቀ።