ከ242 ተሳፋሪዎች አንዲት ነፍስ ብቻ የተረፈችበት የኤር ሕንድ የአውሮፕላን አደጋ።

78

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የበረራ ቁጥሩ 171 የኾነው እና መዳረሻውን ለንደን አድርጎ በረራውን የጀመረው የኤር ሕንድ አየር መንገድ አውሮፕላን 242 ተሳፋሪዎችን እንደያዘ ከ30 ሴኮንድ በረራ በኋላ በምዕራባዊ ሕንድ አሕመድአባድ ከተማ በአስከፊ ኹኔታ መከስከሱ ተሰምቷል፡፡

በዚህ አደጋ የአንድ ሰው ሕይዎት በተዓምር ተርፏለች፡፡ የቤተሰብ ዋልታ እና ማገር የኾኑትንም ቀጥፏል፡ አየር መንገዱ ከ242 ተሳፋሪዎች 241 ሰዎች በአደጋው ሕይዎታቸው ማለፉን እና ከአደጋው በሕይዎት የተረፈ አንድ የእንግሊዝ ዜጋ በሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረገ መኾኑን አስረድቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ከዚህ አደጋ የተረፈው ግለሰብ ቪሽዋኩማር ራሜስ የሚባል ሲኾን ክትትል በሚያደርግበት ሆስፒታል የሕንድ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስትር ያለበትን ኹኔታ በቦታው ተገኝተው መመልከታቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡ የበረራ ይለፍ ማረጋገጫውን ለሪፖርተሮች በማሳየት ተሳፋሪ እንደነበር ያረጋገጠው ራሜሽ አውሮፕላኑ ከተነሳ ከ30 ሴኮንድ በኋላ ከባድ ድምጽ መሰማቱን እና ሁሉም ነገር በቅጽበት እንደተከሰተ ተናግሯል፡፡

በአደጋው ለሕልፈት ከተዳረጉት ውስጥ 169 የሕንድ፣ 53 የእንግሊዝ፣ ሰባቱ የፖርቹጋል እና አንዱ የካናዳ ዜግነት ያላቸው ተሳፋሪዎች እንደነበሩ የቢቢሲ ዘገባ አየር መንገዱን ዋቢ አድርጎ አሳውቋል፡፡

አደጋው በደረሰበት አሕመድአባድ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል የሟቾችን ማንነት የመለየት ሥራ ሲሠራ አምሽቷል፡፡ ኾኖም ግን ከአደጋው አስከፊነት የተነሳ የመለየት ሂደቱ አስቸጋሪ መኾኑን የቢቢሲ ዘገባ ጠቁሟል፡፡ የዘረመል ምርመራ እየተደረገ ቢኾንም ጊዜ እንደሚወስድ ተነግሯል፡፡

በአደጋው ሕይዎታቸውን ካጡ ተሳፋሪዎች ውስጥ የቤተሰቧ ዋልታ ማገር፣ የአባቷ ምትክ፣ የእናቷ ጧሪ እና የወንድሟ አስታማሚ የነበረችው ሲንግሰን ትገኝበታለች፡፡

በአደጋው ሕይዎታቸው ያለፈ ተሳፋሪዎች ልየታ በሚደረግበት በዚህ ሆስፒታል ዙሪያ ከተኮለኮሉ ወዳጅ ዘመዶች መካከል ቢቢሲ በቦታው ተገኝቶ ያናገረው ሆኪፕ ለቤቷ መሠረት የኾነችው ዘመዱ ሲንግሰን የአደጋው ሰለባ መኾኗን ሰምቶ እንደመጣ እና የቤተሰብ አሥተዳዳሪ እንደኾነች ተናግሯል፡፡

“ቤተሰቦቿ ተጨንቀዋል፤ አባቷ ሞቷል፤ እናቷ ብቻ ናት ያለች፣ ወንድሟም የካንሰር በሽተኛ ነው፡፡ ቤተሰቡን የምታሥተዳድር እሷ ብቻ ነበረች፡፡ ቤተሰቦቿ ሙሉ በሙሉ በእርሷ የቆሙ ነበሩ፡፡” በማለት ስለሲንግሰን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡

የአደጋው መንስኤ ምን እንደኾነ ምላሽ ለማግኘት በአውሮፕላኑ የኋለኛው ክፍል የሚገጠመው እና መረጃዎችን ቀርጾ የሚያስቀምጠው ‘ብላክ ቦክስ’ የተባለ መሳሪያ የያዘውን መረጃ ማየት እንደሚያስፈልግ እና ይህ ደግሞ ቀናት ከዛም ሲያልፍ ሳምንታትም ሊወስድ እንደሚችል የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበእገታ እና መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ 33 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“የሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል አሻጋሪ እቅድ አዘጋጅቶ መሥራት ምርጫ ሳይኾን ግዴታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ