በእገታ እና መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ 33 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

21

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእገታ እና መሰል የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ 33 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ አስታውቋል፡፡

ደብረ ብርሃን ከተማ የሰላም ተምሳሌት ኾና ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ነዋሪዎቿም በተደራጀ አግባብ የአካባቢያቸውን ሰላም የማስጠበቅ የዳበረ ልምድ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከማኅበረሰቡ እሴት ባፈነገጠ መልኩ የተደራጀ ስርቆት፣ እገታ እና መሰል ወንጀሎች እየተስተዋሉባት ያለች ከተማ ናት፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያም ወንጀለኞችን በሕግ ቁጥጥር ሥር በማዋል የከተማዋን የተሳለጠ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል እየሠራ ነው። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አበበ የአከራይ ተከራይ ምዝገባ እና ድንገተኛ ፍተሻን ጨምሮ በሕዝብ ጥቆማ መሠረት በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ እንደኾነ ተናግረዋል።

በእገታ እና መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ 33 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ኮማንደር ገብረ መስቀል ቦጋለ ሕዝቡ በተጠናከረ የብሎክ አደረጃጀት አካባቢውን እየጠበቀ መኾኑ የተሻለ የሰላም ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የፖሊስ ተቋሙ የሕዝቡን ድጋፍ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰላምን የማስጠበቅ ተልዕኮውን በአግባቡ ይወጣል ነው ያሉት፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የብሎክ አደረጃጀቶችን ይበልጥ በማጠናከር ከተማዋን ወደነበረችበት የሰላም ተምሳሌትነት የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ይህም የደብረ ብርሃን የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላማቸው መከበር እያደረጉት ያለውን ጥረትም አድንቀዋል፡፡ አሚኮ በከተማዋ በአራት ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ቀበሌዎች በምሽት ተንቀሳቅሶ ባደረገው ምልከታ ማኅበረሰቡ በተጠናከረ የብሎክ አደረጃጀት ሰፈሩን እየጠበቀ እንደኾነ አረጋግጧል፡፡

ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም የጸጥታ አካላት ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ውጤታማ ሊኾን አይችልም ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም ሰፈራቸውን በንቃት በመጠበቅ የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መኾናቸውን ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ: ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠርተዋል።
Next articleከ242 ተሳፋሪዎች አንዲት ነፍስ ብቻ የተረፈችበት የኤር ሕንድ የአውሮፕላን አደጋ።