
ደሴ: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡
ሴቶችን በልማት ኅብረት በማደራጀት እውቀት፣ ጉልበት እና ገንዘባቸውን አሰባስበው የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲጠናከር መሠራቱ ተገልጿል። በገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ በኩልም የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት የተመዘገበባቸው ናቸው ተብሏል። በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎችም ሊሰፉ እና ልምድ ሊቀመርባቸው እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ክልሉ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ኾኖም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ልምድ የሚቀመርባቸው መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የማህጸን በር ካንሰር ክትባት ሥራን በንቅናቄ በመሥራት እና ውጤታማ እንዲኾን በማስቻል በርካታ እናቶች እና ልጃገረዶች ተጠቃሚ በማድረግ አበረታች ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በተቋማት የሕፃናት ማቆያን በማዘጋጀት የመንግሥት ሠራተኛ እናቶች እፎይታ እንዲያገኙ መደረጉ አበረታች እና ሊጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ከነባራዊ የክልሉ ሁኔታ አንፃር አሁንም ቢኾን የፆታዊ፣ የኢኮኖሚ እና አካላዊ ጥቃቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁናዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ 17 የአንድ ማዕከል አገልግሎች ተገንብተው ፆታዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ወገኖች አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ እናቶች ውለው አድረው ሕክምና የሚያገኙባቸው የእናቶች ማቆያ በባሕርዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ከተሞች መጀመራቸውን አንስተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በተቋማቸው በርካታ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢኾን በግጭት ምክንያት በርካታ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ መነጠላቸው እንዳሳሰባቸው እና በልዩ ትኩረት ሕፃናቱን መታደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በጦርነት ምክንያት ለችግር ተጋልጠው ጎዳና የወጡ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅርፍ ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ በርብርብ እና በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን