
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሕክምናው ተጠቃሚ ከኾኑት ውስጥ የሜጫ ወረዳ ነዋሪው መላኩ ወለላ ይገኙበታል። አቶ መላኩ እንደገለጹት ከአምስት ዓመት በፊት አንድ ዐይናቸውን ጉዳት አገጥሟቸው ነበር። በግላቸው በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምና ለማግኘት በመጡበት ወቅት የነጻ ሕክምና ሲሰጥ ይደርሳሉ። አጋጣሚውንም በመጠቀም በነጻ ሕክምና ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ከዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላኛውን ዓይናቸውን ታመሙ። የእድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በአካባቢው የጤና ባለሙያዎች በመነገራቸው በሆስፒታል ተገኝተው ሕክምናውን ማግኘት ችለዋል። የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዐይን ሕክምና ክፍል አሥተባባሪ ድረስ ዓለማየሁ ለ500 ሰዎች ሕክምና ለመስጠት አቅደን 900 ሰዎችን በተለያዩ ወረዳዎች ለይተናል ብለዋል። እስከ አሁን 400 የሚኾኑት አገልግሎቱን አግኝተዋል።
አሥተባባሪው እንዳሉት የዐይን ሞራ ግርዶሽ በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዐይን ሥውርነት የሚያጋልጥ በሽታ ነው። ችግሩ በዘር፣ በእድሜ፣ በአደጋ በመሳሰሉ ምክንያቶች የሚከሰት ነው። በአብዛኛው እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የኾኑ ሰዎች የችግሩ ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። ችግሩን ተከላክሎ ማስቀረት ባይቻልም በቀላሉ መታከም የሚችል ነው። ቀዶ ጥገና ደግሞ ዋናው መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ሆስፒታሉ ከኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በዓመት ሦስት ጊዜ ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና የዘመቻ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። እስከ አሁንም ከ11 ሺህ በላይ የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አሥኪያጅ ዐብይ ፍስሐ እንዳሉት ሆስፒታሉ ባለፉት ዓመታት የዐይን ሞራ ግርዶሽ ነጻ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማኅበረሰቡ እየተሠጠ ይገኛል። የአገልግሎቱ ወጭ ሙሉ በሙሉ በተቋሙ እና በኪዩር ብላይንድነስ የሚሸፈን ነው።
ከሰኔ 02/2017 እስከ ሰኔ 7/2017 ዓ.ም ድረስ ለ500 ሰዎች ሕክምና ለመስጠት ቅድሚያ ቢለይም አሁን ላይ የታካሚዎች ቁጥር በመጨመሩ ቀኑን በማራዘም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ችግሩ ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተቋሙ እንዲገለገሉም መልእክት አስተላልፈዋል። በዘርፉ የሚሠሩ አጋር ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!