
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ የተገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት የሀገር ሽማግሌ ኢያሱ ገጀቦ ግጭትን አስወግደን በሰላም ብንሠራ የጣና ሐይቅ ብቻ ለሀገር የሚበቃ ሃብት ነበር ብለዋል። ወደ ልማት፣ ወደ ሰላም ከገባን ተዝቆ የማያልቅ ሃብት አለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሕዝብ ያደረገልን አቀባበል የሚደንቅ ነው ብለዋል። ደግ ሕዝብ ነው፣ ለዚህ ደግ ሕዝብ ደግሞ የሚገባው ሰላም መኾኑን ነው ያነሱት። በኮንፈረንሱ ለሀገር ጠቃሚ የኾነ የሰላም አጀንዳ መነሳቱን ተናግረዋል። የጋራ የኾነውን የጋራ ችግር በጋራ መፍታት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለምን እንጋጫለን? የሚለውን በመመርመር ለሰላም መሥራት አለብን ብለዋል። በዓድዋ ጦርነት ጊዜ አጼ ምኒልክ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አሰባሰቡ፣ ኢትዮጵያውያንም በጋራ ዘምተው የጋራ ድል አስመዘገቡ፣ ዛሬም የጋራ ድላችን በጋራ እናከብራለን ነው ያሉት።
ዛሬም በሀገራችን ላለው ችግር የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ሁላችንም ይመለከታል ብለዋል። ሀገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅመን ከሠራን ለሀገራችን ሰላም ማምጣት እንችላለን ነው ያሉት። ችግሮችን በጦር መሳሪያ መፍታት እንደማይቻልም ተናግረዋል። የሀገር ሽማግሌዎች ቁርሾ ሳይኖር ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ወደ ሰላም፣ ወደ ውይይት፣ ወደ ሽምግልና እንዲመለሱ እንሻለንም ብለዋል። በኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች በርካታ ችግሮችን መፍታታቸውን አንስተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች ወገናቸው እውነት እና እርቅ መኾኑንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚጠበቅብንን ሁሉ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድ ለአንድነት፣ ለሕዝብ ትስስር እና ሰላም ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል። ከመላው ኢትዮጵያ የተገናኘን ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ በጋራ መክረናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያንን ወክለው ከአዲስ አበባ የመጡት አባት ተሰማ ደሳለኝ ለሀገር ሰላም ትውልዱን በሥነ ምግባር እና በሞራል አንጾ ማሳደግ ይገባል ይላሉ።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሃይማኖት ተቋማት እና በዓለማዊ ትምህርት ቤቶች የሞራል እና የገብረ ገብ ትምህርት በስፋት መሰጠት እንዳለበትም አንስተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እውነተኛ ኾነው ትውልድን ማነጽ እና ማስተማር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አንድ ኾነው ለሰላም ከሠሩ ሰላም እንደሚረጋገጥም ተናግረዋል። ሁሉም ለሀገሩ የተሻለ ነገር ለማድረግ በጋራ መነሳት አለበትም ብለዋል።
ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ በሁሉም አጋጣሚ ሰላምን መስበክ፣ ሰላምን መኖር ይጠበቃል ነው ያሉት። ሃይማኖት እና ሃይማኖተኞች በሚኖሩባት ሀገር ውስጥ ግጭት እንዳይኖር ከልብ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን