“ሰላምን ለማስፈን አማራጭ የሌለው መንገድ ቢኖር የፈጣሪን መንገድ መከተል ነው” ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ

38

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በኮንፈረንሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የሦስተኛው የሰላም ጉባኤ ባማረችው እና ውብ በኾነችው ባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ የተቻለው ሰላም በመኖሩ ነው ብለዋል።

የሰላም ዋጋ ተነግሮ እና ተዘክሮ እንደማያልቅ የጠቆሙት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም “በቃል ሰላም እያልን እንናገራለን በተግባር ለሰላም ያለውን ሁኔታ እንፈትሽ” ነው ያሉት። ሼሁም፣ ቄሱም፣ ወጣቱም፣ ባለስልጣናቱም፣ ሕጻናቱም ኾነ ሴት ወንዱ በየማዕረጉ ሰላም ላይ ያለውን ሁኔታ ገምግሞ ምን አስተዋጽኦ አደረኩ የሚለውን እንዲያይ አመላክተዋል።

ችግሮች ከሰማይ እንደማይመጡ እና ከምድርም እንደማይበቅሉ የተናገሩት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ችግሩ የሚመጣው ከእኛው ነው ብለዋል፡፡ ሰላም የሚጠፋው እና ፈተና የሚከሰተው፣ ወንጀሎች የሚፈጠሩት በሰው ልጆች መኾኑንም አብራርተዋል፡፡ ሁሉም በፈጣሪው መንገድ ቢመራ እና ቢተዳደር ፈተናዎች ሊከሰቱ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም ሰው ፍትሐዊ ሥራ ቢሠራ እና በፍትሕ ቢተዳደር ችግሮች እንዳማይኖሩም ገልጸዋል። “ሰላምን ለማስፈን አማራጭ የሌለው መንገድ ቢኖር የፈጣሪን መንገድ መከተል ነው” ብለዋል። ሀገርን ሁለት ነገሮች ጎድተዋታል ያሉት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም እነዚህም ድህነት እና ሰላም ማጣት ናቸው ነው ያሉት።

ሀገርን የጎዱ እነዚህ ጉዳዮች የሚነሱት ከድህነት እንደኾነ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሥልጣን ሽግግሩ በመሳሪያ በመኾኑ አንዱ ሲገነባ ሌላው እያፈረሰ ሁሌ ኢትዮጵያ ድሀ ሁና መኖሯን ነው ያስታወሱት። የሕዝብ ብዛታችን ጥቅም ሳይሰጠን ሌሎች ከኢትዮጵያ ያነሱ ሀገራት አንድ ሁነው ወደ ልማት በመሰለፍ በልጽገው እኛ መቼ ነው እንደነዚህ ሀገራት አንድ ኾነን የምንበለጽገው የሚል ምኞት ውስጥ ገብተናል ነው ያሉት።

አለመግባባት ለሰላም ጠንቅ ኾኗል ያሉት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ይህንንም ማረጋገጥ የሚቻለው በመሳሪያ ሳይኾን በመነጋገር እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ ችግሮች ሁሌም የሚፈቱት በንግግር፣ በውይይት በመኾኑ ሁሉም በሀገራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ ችግሮችን እንዲፈታ አሳስበዋል፡፡

ማንኛውም ያኮረፈ፣ የተቸገረ እና የከፋው አካል ሁሉ ወደ ሀጋራዊ ምክክሩ በመምጣት ችግሮችን ፈትቶ የሀገርን ሕመም እንዲያክምም ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሁሌም ድሀ ሀገር ተብላ እንዳትጠራ በቃ ማለት እንደሚገባ እና ችግርን ተቀራርቦ በመፍታት ወደ ልማት፣ ወደ ዕድገት እና ከፍ ወዳለ ማማ ላይ ማውጣት ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ መምህራን ጋር ተወያዩ።