ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች

12

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ተቀብላ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 16 ላይ እንደተገለጸው ማንም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት ያለው መኾኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሴቶችን የሚጨቁኑ፣ በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎች እና ልማዶች የተከለከሉ እንደኾኑም ተመላክቷል፡፡

እነዚህ ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል እንደኾኑ እና በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱት መሠረታዊ መብቶችም ከእነዚህ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 እና በአንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 ስር በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡

በአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ደመቀ ይብሬ እነዚህን መሠረታዊ መብቶችን ከሚጥሱ ድርጊቶች ውስጥ አንዱ ጾታዊ ጥቃት ይጠቀሳል ይላሉ፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እነደኾነ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት ዕውቅና የተሰጠው እ.ኤ.አ 1979 የወጣው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት አድልኦ ለማስወገድ የተደረገው ቃልኪዳን እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጅ ይላሉ አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃት ምን ማለት እንደኾነ የሚተረጉም ግልጽ የሕግ ድንጋጌ ግን አልተቀመጠም ነው ያሉት፡፡ በተግባርም ጾታዊ ጥቃት፣ ጾታዊ ትንኮሳ እና አስገድዶ መድፈር የሚሉትን ቃላት በተደበላለቀ መልኩ መረዳት ይስተዋላል ብለዋል፡፡ እነዚህ ቃላት በተወሰነ መልኩ የሚገናኙ ቢኾንም የተለያዬ ትርጉም አላቸው ነው ያሉት፡፡ ጾታዊ ጥቃት ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ ሲኾን ጾታን መሠረት ባደረገ መልኩ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ሁሉ ያካትታል ብለዋል፡፡

ጾታዊ ጥቃት ማለት በጥቅሉ ኀይል በመጠቀም (በማስገደድ፣ በማስፈራራት እና በማታለል) ወይም ያለፍላጎት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ድርጊት ስለመኾኑ አብራርተዋል፡፡ ይህም ጥቃት በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ሲኾን አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ሊኾን ይችላል ብለዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መኾኑን ጥናቶች ያሳያሉ ይላሉ አቶ ደመቀ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርትም በዓለማችን ከ3 ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይደርሳል ነው ያሉት፡፡

ከሁሉም የከፋ የሚኾነው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ማኅበራዊ መገለልን በመፍራት፣ የበቀል ርምጃን በመፍራት፣ በፍትሕ አካላት ላይ ዕምነት በማጣት አብዛኛው ጾታዊ ጥቃቶች ለፍትሕ አካላት ሪፖርት የማይደረጉ መኾኑን መረጃዎች እንደሚያሳዩም ነው የገለጹት፡፡

ጾታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው 10 ሴቶች መካከል ወደ ፍትሕ ተቋማት ሪፖርት የምታደርገው አንዷ ብቻ እንደኾነች ጥናቱ ያሳያል ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እና በተናጠል ሰፊ ጥረት ቢያደርጉም መሠረታዊ በኾነ መልኩ ጥቃቶቹን መቀነስ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች ያሉ ሲኾን ከችግሮቹ አንዱ ከሕግ ክፍተት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ ለአብነትም የሕጎች ግልጽነት አለመኖር፣ አሻሚ ትርጉም መኖር፣ የቅጣት ማነስ እና አስተማሪ አለመኾን ይጠቀሳሉ ነው ያሉት፡፡

ለአብነት ብለው ያነሱት አቶ ደመቀ ከጾታዊ ጥቃቶች አንዱ የኾነውን ወሲባዊ ትንኮሳ በተመለከተ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 625 በከፊል የተመለከተ ቢኾንም በድንጋጌው ውስጥ ተካቶ የሚገኘው ሥልጣን፣ ኀላፊነት ወይም ችሎታ ባላቸው ግለሰቦች የሚፈጸም ወሲባዊ ትንኮሳ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

ስለኾነም ሥልጣን በሌላቸው ግለሰቦች ማለትም በሥራ ባልደረቦች፣ በጓደኞች ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው የሚፈጸምን ወሲባዊ ትንኮሳ አላካተተም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በድንጋጌው ውስጥ “ከፍ ያለ ቁሳዊ ችግር ወይም የህሊና ሀዘን” እንዲሁም “ለንጽህና ተቃራኒ የኾነ ድርጊት” የሚለው አገላለጽ አሻሚ እና ግልጽነት የጎደለው በመኾኑ ወጥነት ያለው አሠራር እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል፡፡ ሌላው በትዳር ውስጥ ያሉ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው እንዲሁም በወንድ ጓደኞቻቸው የሚደርስባቸው ጥቃት በወንጀል ሕጉ በግልጽ ተመላክቶ አይገኝም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በትዳር አጋር የሚፈጸም የቤት ውስጥ ጥቃት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በወንጀል ሕጉ ውስጥ አስገድዶ መድፈር በወንጀልነት ተደንግጎ ቢገኝም አስገድዶ መድፈር ምን ማለት እንደኾነ እንዲሁም ምን ምን ሁኔታዎችን እንደሚያካትት የማይገልጽ በመኾኑ በሕጉ አተገባበር ረገድ ክፍተቶች ይሰተዋላሉ ነው ያሉት፡፡ ለአብነትም አስገድዶ መድፈርን ከድንግልና መወሰድ ጋር ብቻ ማያያዝ አልፎ አልፎ ይታያል ይላሉ፡፡

አብዛኛው ጾታዊ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ሰዎች ሊያዩ እና ሊሰሙ በማይችሉበት ጊዜ እና ቦታ በመኾኑ ማስረጃዎችን እንደልብ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተጎጅዎች ፍትሕ ሳያገኙ የሚቀሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ነው ያሉት፡፡

ከወንጀል ሕጉ ባሻገር በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት ጾታዊ ትንኮሳ የተፈጸመበት ሠራተኛ የሥራ ቅጥር ውልን ያለማስጠንቀቂያ የማቋረጥ እና የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት ያለው መኾኑ የተደነገገ ቢኾንም ስለ ውሉ መቋረጥ እና ስለሚያስከትለው ውጤት ከመግለጽ በስተቀር ትንኮሳውን የሚቀጣ አይደለም ብለዋል፡፡

ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባት ሴት የሚኖራት የመጀመሪያው መፍትሔ የአጥፊውን የወንጀል ተጠያቂነት ማረጋገጥ እና ተጎጅዋ ፍትሕ እንድታገኝ ማስቻል ሲኾን በፍትሐብሔር ደግሞ የህሊና ጉዳት ካሳ እንዲሁም ለደረሰባት ቁሳዊ ጉዳት ተመጣጣኝ የኾነ ካሳ የማግኘት መብት ይገኝበታል ነው ያሉት፡፡

ተጎጅዎች የካሳ ጥያቄውን በራሳቸው አቅም ለማቅረብ የማይችሉ ከኾነም በየደረጃው የሚገኝ የዓቃቤ ሕግ ተቋም በወንጀል ሰለባ ለኾኑ ተጎጅዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ የማድረግ ኀላፊነት የተሰጠው በመኾኑ ድጋፍ ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡

በሥራ ቦታ ላይ የሚፈጸምን ጾታዊ ጥቃት በተመለከተ ደግሞ በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጁ እንዲሁም በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ የተቀመጡ መፍትሔዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል በዘርፉ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መስጠት፣ የሚመለከታቸውን እና የአጋር አካላትን ትብብር ማጠናከር እና ትኩረት አድርጎ መሥራት አስፈላጊ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ከቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ብጹዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ
Next article“ሰላምን ለማስፈን አማራጭ የሌለው መንገድ ቢኖር የፈጣሪን መንገድ መከተል ነው” ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ