“ቀኑ ፈጽሞ ሳይመሽ ሃይማኖትን ከፖለቲካ፣ ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳንቀይጥ ለሰላም እንቁም” ብጹዕ አቡነ አብርሃም

46

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም በዕለቱ ተገኝተው አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም እና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን ብለዋል በንግግር መግቢያቸው ላይ። እግዚአብሔር ከሚለው በላይ የለም እና እውነተኛ ሰላምን ለማግኘት እግዚአብሔር የሚለውን መስማት አስፈላጊነቱን አስገንዝበዋል። እግዚአብሔር የሚለውን መስማት ያጽናናል፤ እግዚአብሔር የሚለውን መስማት ያረጋጋል ነው ያሉት።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የሰላም አምላክ የኾነውን እግዚአብሔርን መስማት እውነተኛ ሰላምን ለማግኘት፣ በሰላም ለመኖር፣ ለአማራጭ የማይቀርብ ፍቱን መድኃኒት መኾኑን ያረጋግጥልናል ብለዋል። ስለ ሰላም ምሁራኑ ብዙ ጽፈዋል፣ ተናግረዋል፣ አሠልጥነዋል ብለዋል። ኀያላኑም ሰላምን በጦር ለማስፈን ብዙ ደክመዋል ጥረዋል ነው ያሉት። ይሁን እንጅ በዚህ መንገድ የሚፈጠር ሰላም ብልጭ ድርግም የሚል እና ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ የማይችል እንደኾነ ነው የተናገሩት።

አለመሳካቱ አድካሚ ከመኾኑም በላይ የንጹሐንን ሕይወት የሚያሳጣ፤ ሀብት ንብረት የሚያወድም፤ ትውልድን በብዙ ነገር የሚጎዳ እንደኾነ ከሀገራችን ጀምሮ በዓለም ዙሪያም በተግባር እያየን ነው ብለዋል። ትናንት ውበትን ተጎናጽፈው የነበሩ ከተሞች ዛሬ ላይ ምን እንደሚመስሉ ሁላችንም የዐይን ምስክሮች ነን ነው ያሉት ብጹዕነታቸው። ስለዚህ ሰላምን ለማግኘት፣ የሰላም አየር ለመተንፈስ እግዚአብሔር የሚናገረውን እሰማለሁ ማለትን መልመድ አለብን ብለዋል።

ሰላምን ፈላጊ እስከኾን ድረስ ልባችን የግጭትን፣ የጦርነትን፣ የመለያየትን እና የእልክን ሀሳብ መሰረዝ ይገባል ነው ያሉት። ወደ እግዚአብሔር መመለስ የመጀመሪያው ርምጃችን መኾን እንዳለበትም ገልጸዋል። ይህ ሲኾን የሰው ልጅ ገርነትን ገንዘቡ ያደርጋል ነው ያሉት። ከመልካም ፍሬዎች አንዱ ገርነት ነውና ብለዋል።

የልብ ደስታ ሰላም ነው፣ ከሰላም ውጭ የሚገኝ ድል እና ደስታ ጸጸት እና እሮሮ የማይለየው እንደኾነም ተናግረዋል። ስለኾነም ካላስፈላጊ ጸጸት ለመዳን፣ የታሪክ ተወቃሽ እና የትውልድ ተጠያቂ ላለመኾን የሁሉንም ወገን ቅንነት ይጠይቃል ነው ያሉት። አበው ካነጋገር ይፈረዳል፤ ካያያዝ ይቀደዳል እንዲሉ ለሰላም እንቅፋት እና መሰናክል ከሚኾን የአነጋገር ፈሊጥ ጥንቃቄ ማድረግ የሰላም ፈላጊ ትልቁ ድርሻ ነው ብለዋል ብጹዕነታቸው።

ለሀገራችን ሰላም መታጣት አንዱ ምክንያት የሚወረወር የከንፈር ፍላጻ ነው ብለዋል። ይህም ለኢትዮጵያዊያን እንግዳ ነገር እና ህሊናን የሚያቆስል እንደኾነም ነው የጠቆሙት። ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከማይመጥን ጸብ አጫሪ እና ጥላቻ አንጋሽ ንግግር መቆጠብ የዕለት ከዕለት አንዱ ሥራችን መኾን አለበት፤ ያን ጊዜ ውድቀታችን የማይሻ የሁላችን አምላክ በዐይነ ምህረቱ ይመለከተናል ነው ያሉት።

ከኛ የሚጠበቀው ከክፉ ሥራዎች መራቅ እና እግዚአብሔርን ደጅ መጥናት መኾን እንዳለበትም ነው የገለጹት። ይህ ዘመን ለኛ ለሃይማኖት መሪዎች ራስ ምታት፣ የልብ ስብራት ነው ብለዋል። ምክነያቱም ሀዘናችን ቅጥ አጥቷል ሲሉም ነው ብጹዕነታቸው የተናገሩት። ተሰሚነታችን እና ተደማጭነታችን ወደ ኋላ መለስ ብለን ከአባቶቻችን ጋር ካነጻጸርነው ቁልቁለት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።

ገዳዮችም፣ ተገዳዮችም፣ ተፈናቃዮችም፣ አፈናቃዮችም፣ ተሳዳጆችም፣ አሳዳጆችም የኛ ልጆች ናቸውና ብለዋል። እንደ አባቶቻችን ልንሠራ የሚገባውን ባለመሥራታችን ወገኖቻችን ተቸግረውብን ይገኛሉ ነው ያሉት። ስለዚህ “ቀኑ ፈጽሞ ሳይመሽ ሃይማኖትን ከፓለቲካ፣ ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳንቀይጥ ለሰላም እንቁም” ብለዋል።

ልባችን ከእሰጥ አገባ ተላቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችን እንፈታ ዘንድ አደራ የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“አንዳችን ያለ ሌላው ጎደሎ ነን” ቄስ ደረጀ ጀንበሩ
Next articleለርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሜዳሊያ ሽልማት ተበረከተ።