“አንዳችን ያለ ሌላው ጎደሎ ነን” ቄስ ደረጀ ጀንበሩ

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ሁላችንም ዛሬ እንድንሰባሰብ ያስገደደን ነገር የኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ ነው ብለዋል ።

ሰላም በማንኛውም ቁሳዊ ነገር የማይተካ ነው ያሉት ቄስ ደረጀ ከድህነት መውጣት የሚያስችለን ወሳኙ ነገር ሰላም ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በእርስ በእርስ ግጭት የተነሳ ብዙ ጉዳት አስተናግዳለች ያሉት ቄስ ደረጀ በዋናነትም ለድህነታችን እና ወደ ኋላ ለመቅረታችን ምክንያቱ ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ የጦር መሣሪያ በማንሳት መጠፋፋት ላይ በማተኮራችን ነው ብለዋል።

አንዱ በሌላው ላይ ያስከተለው ጉዳት ጥላቻን ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማሸጋገር እና የሕዝባችንን ሰቆቃ ከማባባስ በስተቀር መልካም ነገር አላስገኘም ነው ያሉት። ይህ እየታወቀ አኹንም ከመጠፋፋት አዙሪት ለመውጣት የምናሳየው ፈቃደኝነት አለመኖር ወይም አዝጋሚ መኾን እጅግ ያሳዝናል ብለዋል።
የችግሩ መፍትሔ ያለው በእኛው እጅ ስለኾነ ችግሩ ተባብሶ ጥፋት ሳያስከትል ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ አለብንም ነው ያሉት።

በፍጹም ቅንነት የሰላም ጭላንጭል እንዳይደበዝዝ ይልቁንም ደምቆ እንዲበራ እና ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ለመኾን ጦርነትን በቃን በማለት ማንኛውንም ልዩነት በውይይት እና ዕርቅ ብቻ እንዲፈታ የሚቻለንን ሁሉ እናበርክት ብለዋል። በጉልበት የሚደረግ እንቅስቃሴ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነውም ብለዋል። በመኾኑም ሁሉም በሰከነ መንፈስ ልዩነቶችን በውይይት እንፍታ ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ለሀገር አንድነት እና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለሕዝባችን ፍቅር ርህራሄ ልናደርግለት ይገባል ሲሉም ተማጽነዋል። ከእንግዲህ የሕዝብን ሰቆቃ ላለመስማት እና ላለማየት ከጉልበት እና መሣሪያ ይልቅ ውይይትን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

“አንዳችን ያለ ሌላው ጎደሎ ነን” ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው ብርታት የሚገኘው በሰላም ስለኾነ በአንድነት እንቁም ብለዋል። የሀገራችንን ሰላም እንመልስ ነው ያሉት። መሳሪያ አንግበው የወጡ ወንድሞቻችን ወደ ሰላም ይመለሱ ዘንድም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረጉ የትጥቅ ትግሎች ኢትዮጵያውያንን ዋጋ እያስከፈሉ ነው ሲሉ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።
Next article“ቀኑ ፈጽሞ ሳይመሽ ሃይማኖትን ከፖለቲካ፣ ፖለቲካን ከሃይማኖት ሳንቀይጥ ለሰላም እንቁም” ብጹዕ አቡነ አብርሃም