
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ”ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ባስተላለፉት መልዕክት አማራ ክልል ያሉት የቱሪስት መስህቦች እና ማዕድናት በርካታ መኾናቸውን ገልጸው ለጉብኝት የሚመረጥ ክልል መኾኑንም አንስተዋል።
ይህንን የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ ለመጠቀም መተባበር እና ሰላምን ማስፈን እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ሦስተኛው ሀገራዊ ጉባኤ በባሕር ዳር ሲካሄድም የክልሉን ሰላም የማጽናት ታላቅ ጥረት የማገዝ ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል።
ሰላም የመገንባት ሥራን የሁሉም ተግባራት ማዕከል ማድረግ ይጠበቅብናል። የሃይማኖቶች አስተምህሮ ስለ ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮነት እንዲሁም የሰዋዊ ግንኙነት መርሆቻቸው ተመሳሳይነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ጉባኤውም የሃይማኖቶችን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን በማጎልበት ዜጎች ከእምነታዊ ድንጋጌዎቻቸው በመነሳት የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በትብብር እና በመከባበር እንዲኖሩ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሃይማኖቶች የሚያስተምሩት መተሳሰብ እና በትህትና ሌላውን ማክበር እንደኾነም አንስተዋል። አንዳንድ ሰባኪዎች ግን ከአስተምህሮቻቸው የሚቃረኑ መልዕክቶችን በማጣቀስ ችግር እንደሚፈጥሩ አንስተዋል። ከሃይማኖታዊ ይልቅ ዓለማዊ ሃሳቦች የተጫኗቸው መልዕክቶች ሲተላለፉ ጤናማ ያልኾነ ውድድር እና ፉክክር በመፍጠርም ለሰላም ጠንቅ መኾኑን ጉባኤው ጠቅሶ ሲያወግዝ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአማኞች ሀገር ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ግፍ እና ለሰዎች እየተሰጠ ያለው ስያሜ፣ የሃይማኖት ተቋማት መቃጠል፣ የሃይማኖት መሪዎች መገደል እና መንገላታት፣ የሰዎች መታገት የሰላም ጠንቅነቱን ገልጸዋል። አንዳንድ የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው አካላት ችግሮችን በሰላም እና በውይይት ከመፍታት ይልቅ በኃይል ለመፍታት የሚያደርጉት የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያውያንን አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለ መኾኑን አንስተዋል።
ሁሉም ወገኖች ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት እና ድርድር እንዲፈቱም ሲጠየቅ መቆየቱን አንስተዋል። የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ የክልሉ ታጣቂ ኃይሎችም ለሰላም እና ለውይይት እንዲቀርቡ በጉባኤው ሥም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
መንግሥትም እንደ ሀገር ሰላምን ለማጽናት የጀመረውን ሁለንተናዊ ጥረት እንዲያጠናክር በጉባኤው ስም አሳስበዋል። መላ ኢትዮጵያውያንም በሃይማኖት፣ በብሔር እና በሥራ ስምሪት ሳይለያዩ ጦርነትን በቃኝ እንዲሉ ጠይቀዋል። ጥላቻን እና ጦርነትን በመጠየፍ፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አሉታዊ መልዕክቶች ባለመቀበል ለሰላም የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
ሰላምን የምንጊዜም ምርጫችን በማድረግ ሰላማዊነትን እናጠናክር እና የሀገራችን የሰላም ምሰሶ እንድናጸና ጉባዔው ጥሪውን ያቀርባል ብለዋል። የጉባኤው ዓላማ በሀገራችን ያለውን የሰላም እጦት እና ያለመረጋጋት በዘላቂነት በመፍታት ለሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማነሳሳት መኾኑን አንስተዋል። ዓላማው እንዲሳካም የሁሉም ሰላም ወዳድ ኃይሎችን ቀና ትብብር አስፈላጊነት አንስተዋል።
የሰላም ግንባታ ሥራ የረጅም ጊዜ ሂደት እና የተለያዩ አካላትን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አንስተው የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ምዕመናን የየአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ አዎንታዊ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን