
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ድንቅ ሀገር መኾኗን አስታውሰዋል።
የእምነት ተቋማት ማንነቶቻችን ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ ስትከፋ ተከፍታ እና ታቦቶቿን ይዛ ሀገር ስትገነባ ነው የኖረችው። በአውደ ምኅረቷም ኢትዮጵያን እግዚብሔር ይጠብቃት ዘንድ ተግታለች ነው ያሉት።
የእስልምና ሃይማኖትም ማንነት ኾኖ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ያጸና ነው ብለዋል። ወንጌላውያንም በኢትዮጵያ ጉዳይ በሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚና እየተጫዎተ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
የካቶሊኩም ኾነ የሰባት ቀናት አድቬንቲስትም በአጠቃላይ ሁሉም በደም፣ ሥጋ እና አጥንት እየተገናኘ ነገር ግን አንዲቷ መርከብ ላይ ቁጭ ብለን የምንወዳትን እና ለምትወደን ሀገራችን ሰላም እንድትኾን መስዋዕት ልንከፍል ይገባል ብለዋል።
መላ ሕዝቡ ወደ እምነት ተቋማቱ ሲመላለስ ልንሰማው፣ ልናልመው እና ልንተገብረው የሚገባ ጉዳይ ሰላም ብቻ መኾኑን ዶክተር ከይረዲን ተናግረዋል።
ሁሌም የሃይማኖት አባቶች ” እኛን እየገሰጻችሁ፣ ወጣቱን እየመከራችሁ ከዚህ ላደረሳችሁት ወጣት ውይይትን እና መመካከርን በማስቀደም የተጀመረው የሰላም ሥራ ሊጠናከር ይገባዋል ነው ያሉት። ከምንሽር ይልቅ ምክክር መቅደም አለበት ነው ያሉት።
እዚህም እዚያም የገጠሙን ችግሮች ከእምነቶቻችን ሕልም ጋር አይሄድምና ትናንት አመላቸውን በጉያ ስንቃቸውን በአህያ ጭነው ይህችን ሀገር እንዳስረከቡን ቅድመ አያቶቻችን እኛም ሰላማዊ ኢትዮጵያን ልናስረክብ ይገባናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠባቂዎች እኛ ነን ያሉት ዶክተር ከይረዲን ተመካክረን ማጽናት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን