
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የዘጠኝ ወራት የመሠረተ ልማት ዘርፍ እቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግመዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዘርፉ 6 ሺህ 73 አነስተኛ የገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ 716 ብቻ ተሠርተዋል፡፡ አፈጻጸሙም 11 በመቶ ብቻ ነው፡፡ አጠቃላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት አሁንም በብዙ ከተሞች ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ቢሆንም ከነበረው በአንድ በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 92 ነጥብ 19 መድረሱ በሪፖርቱ ቀርቧል።
በመስኖ ልማት 1ሺህ 970 ሄክታር የሚያለሙ 11 ፕሮጀክቶች የጥናት ዲዛይን ሲሠራ ስድስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁ ተገልጿል። በመንገድና ትራንስፖርት ዘርፍ በክልሉ በዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 490 ኪሎ ሜትር ወቅታዊና መደበኛ ጥገና ለማካሄድ ታቅዶ 58 ነጥብ 7 በመቶ እንደተፈጸመ ተገምግሟል። በዘጠኝ ወራት የመንገድ ግንባታ አፈጻጸም የቅዱን ግማሽ ብቻ እንዳለው ተመላክቷል፡፡ በዕቅዱ የተያዙ አምስት ድልድዮች መገንባታቸው ደግሞ በስኬት ተጠቅሷል፡፡
በክልሉ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እቅድ ቢያዝም በዕቅዱ ከተያዙት 46 ሺህ 11 ህገወጥ ግንባታዎች ማፍረስ የተቻለው 3 ሺህ 436 ብቻ ነው። በ25 ከተሞች ሳይንሳዊና የተቀናጀ የከተሞች ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ለመፈጸም የተያዘው እቅድም በስምንት ከተሞች 32 በመቶ ብቻ እንደተፈጠመ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በዓመቱ ለ 1ሺህ 700 የመኖሪያ ቤት ሥራ ማኅበራት 600 ሄክታር ቦታ ለመስጠት ታቅዶ አፈጻጸሙ 59 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ በባሕር ዳር፣ ጎንደርና ደሴ ከተሞች ቦታ ባለመኖሩ ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መዝለቁም በሪፖርቱ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
