
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው። ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ” ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በኮንፈረንሱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ፋሲል ታዬ የዛሬው ኮንፈረንስ ከኮንፈረንስ በላይ ነው ብለዋል። የለውጥ ነጥብ ነውና ነው ያሉት። “በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር ጽኑ እምነት እየተመራን ከቁጣ ሳይኾን ከተስፋ ጋር የተሰባሰብንበት ወቅት ነው” ብለዋል።
በፍርሃት ሳይኾን በድፍረት፣ መለያየትን ለመዝራት ሳይኾን አንድነትን ለመገንባት ነው የተሰባሰበው ነው ያሉት። የደበዘዘብን ሰላም የምናጎላበት፣ የሰላም ጥሪያችንን የምናቀርብበት መቀራርብን እና መተማመንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ የምናደርግበት መድረክ ነው ብለዋል። “ሃይማኖት እና ሃይማኖተኝነታችን ከገጠመን ቁስል የምንፈወስበትን ጥበብ የምንጎናጸፍበት ታላቅ ሃብታችን ነው” ያሉት ጸሐፊው ይህ ሃይማኖተኝነታችን ከፈጣሪ፣ ከሁሉም ፍጡራን እና ከተፈጥሮ ጋር ሰላማዊ እና በበጎ የመተሳሰብ ተዛምዶ አንዲኖረን የግድ ይለናል ነው ያሉት።
የክርስትናም ኾነ የእስልምና አስተምህሮት እና ወጎቻችን ሰላም የተቀደሰ ተግባር እና ግብ መኾኑን፣ የሰው ልጅ ሕይዎትም በጣም የከበረ እና ውድ እንደኾነ እና ፍትሕ የማንኛውም ዘላቂ አንድነት መሠረት እንደኾነ ያስተምሩናል ብለዋል በመልዕክታቸው። እንደ ተለያዩ ሃይማኖቶች ባለቤትነታችን እና ብዝኀነታችን በተለያዩ መንገዶች የምንጸልይ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የምንናገር፣ በተለያዩ ባሕላዊ አኗኗሮች የምንገለጽ ቢኾንም የርኅራኄ፣ የእውነት፣ የፍትሕ እና የፍቅር እሴቶቻችን አንድ ያደርጉናል ነው ያሉት።
እነዚህን እሴቶቻችን መንከባከብ እና መጠበቅ ደግሞ የተውልዱ ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል። የሃይማኖት፣ የማኅበረሰብ እና የሕዝብ መሪዎች ተቀዳሚ ኀላፊነት እንደኾነም አንስተዋል። የአማራ ክልል በብዝኀነት የበለጸገ መኾኑን ያነሱት ጸሐፊው የተለያዩ ብሔረሰቦች እውቅና አግኝተው የራሳቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደር መሥርተው የሚኖሩባት፣ በርካታ ቋንቋዎች የሚነገሩበት እና ብዙ ሃይማኖቶች የሚመለኩበት መኾኑን ገልጸዋል።
ብዝኀነታችን ደግሞ ስጋት ወይም ድክመታችን ሳይኾን ጥንካሬያችን እና ውበታችን ነው ብለዋል። ብዝኀነታችን የተጣለብን እና ችለን የምንኖረው ወይም የምንታገሰው ሸክም አይደለም፣ በፍቅር አቅፈን የምንይዘው ስጦታችን እና ማንነታችን ነው፤ ልጆቻችን በነዚህ ልዩነቶቻቸው ውስጥ ያሉ አንድነቶችን እንዲያውቁ እና እንዲያጠነክሩ እናስተምራቸው ነው ያሉት። የሃይማኖት ሰዎች በሃይማኖት፤ በፖለቲካ ወይም በጎሣ ስም የሚፈጸም ጥቃትን በግልፅ እና በዓደባባይ ልንቃወም እና ልንከላከል ይገባል ብለዋል።
የትኛውም ሃይማኖት ጥላቻን አይሰብክም፣ በልዩነቶቻችን ውስጥ እንደ ድልድይ ኾነው የሚያገናኙንን እሴቶች ለማፈራረስ የሚሰነዘሩ በሃይማቶች፣ በብሔር እና በሌሎች ማነንቶች ላይ የተመሠረቱ የጥላቻ ቃላትን እና ተግባራትን በየደረጃው ልንቃዎም ይገባል ነው ያሉት።
መሪዎች ሰላም ከተናገርን ሕዝባችን በሰላም መንገድ ይሄዳል፣ ጥላቻን እና ንቀትን የምንናገር ከኾነም በተመሳሳይ ብዙዎች በጥፋት መንገድ እንዲጓዙ ያደረጋል ብለዋል። ምሬትን ሳይኾን ጥበብን፣ ትዕግስትን እና ይቅር የማለትን ድፍረት በትውልዳችን እናስርጽ ነው ያሉት።
እውነተኛ ሰላም ለማስፈን በእውነት እና በመተማማን መነጋገር እና መወያየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። እዚህም እዚያም ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እና አውነተኛ ፈውስ ለማምጣት ጠንካራ የምክክር መድረኮችን ለመፍጠር የሃይማኖት መሪዎች እና የማኅበረስቦች መሪዎች በዋናነት ሊያተኩሩበት የሚገባ ዐቢይ አጀንዳ መኾኑን አንስተዋል።
በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን በመተማመን እና በመገነዛዘብ የተመሠረቱ ውጤታማ ውይይቶች እንዲያደርጉ ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔም ይህንን ዓላማ ለመደገፍ እና እንደ ድልድይ ለማገልገል ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።
“ሀገር በስስት እና በተስፋ የሚያያችሁ፤ የነገ እድላችን በእጃችሁ ላይ የወደቀው ወጣቶች የትውልዱ ዐይን እና ተስፋ በእንናት ላይ ነው” ብለዋል። በየትኛውም የሕይዎታቸው አጋጣሚ የጥላቻ መሳሪያ እንዳይኾኑ አሳስበዋል።
ሙሉ ኃይላቸውን ለበለጠ ቁም ነገር፣ ለእውቀት፣ ለጥበብ፤ ለሰላም፣ ለውይይት፣ የፈረሰውን መልሶ ለመገንባት እንዲያወወሉትም አሳስበዋል። ኮንፈረንሱ በአማራ ክልል በሰላም እንዲከበር ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን