“ሀገር የትውልዶች ውጣ ውረድ የእጅ ሥራ ናት” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ ሰላማዊ ውይይት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት ሚና በሚል ርእሰ ጥናት ያቀረቡት የሕግ ተመራማሪው ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የሃይማኖት ተቋማት ሀገር የገነቡ ናቸው ብለዋል። አኹንም ሀገርን የማስቀጠል ትልቅ ሚና አላቸው ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ታሪክ ያላቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ሀገረ መንግሥት ሃይማኖትን እና መንግሥትን የሚያስተሳስር ትልቅ የሀሳብ እና የተግባር ጥምረት ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ በሃይማኖት እና በፖለቲካ መካከል ያለው መስተጋብር የሀገሪቱን ሕዝብ ባሕላዊ ገጽታ በመቅረጽ ጉልህ ሚና አለው ነው የሚሉት። ሀገረ መንግሥት ግንባታ ከሕዝብ፣ ከመንግሥት እና ከሃይማኖት መስተጋብር ውጭ ማሰብ አይቻልም ይላሉ።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደታችን ውስጥ ስኬትም፣ ውድቀትም ገጥሞናል፣ ስኬቶቻችንም፣ ውድቀቶቻችንም የጋራ ናቸው፣ አኹን ካለንበት ችግር የምንወጣውም በጋራ ነው ብለዋል። ሰላም እና እርቅን ዋና መውጫ መንገድ ለማድረግ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ላቅ ያለ ነው ብለዋል። “ሀገር የትውልዶች ውጣ ውረድ የእጅ ሥራ ናት” ሀገር የሕዝቦቿ፣ የእምነት፣ የጋራ ድካም እና ውጤት ናት”ነው የሚሉት።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ልምምድ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗንም ገልጸዋል። ብዙዎቹ የዓለም ሀገራት ከቅኝ ገዢ የወጡበትን እንደ ታሪካዊ ቀን ሲወስዱ ኢትዮጵያ ግን የድል ቀንን ታከብራለች ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ የዘለቀች፣ የጥንታዊት ሥልጣኔ ባለቤት የኾነች፣ የአፍሪካ እንቁ ናት ብለዋል። የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤቶች ሁሉ ጥንታዊነታቸውን አላስቀጠሉም፣ ታይተው የጠፉ ሥልጣኔዎች አሉ፣ እኛም ታይተን እንዳንጣፋ፣ ያለንን ታሪክ ለማስቀጠል፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት መታገል አለብን ነው የሚሉት።

በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የተነሱ መሪዎች ሕዝባቸውን አሥተባብረው፣ ነጻነትን አስከብረው ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል። ይህም ታሪክ እንደ ተራራ የገዘፈ አኩሪ ታሪክ ነው ብለዋል። ይህ የገዘፈ ታሪክ የመጣው ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ቋንቋ ሳይገድባቸው ከመሪዎቻቸው ጎን ተሰልፈው አኩሪ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ነው ብለዋል።

ጥንታዊቷን እና ጠንካራዋን ኢትዮጵያን ድክመቷን አክመን፣ ጥንካሬዋን ለማስቀጠል ጀግንነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ በሀገር መኩራት፣ የሀገር ፍቅር እና መተሳሰብ ያስፈልገናል ነው ያሉት። የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሀገር፣ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መኖር ስለሚገባው መልካም መሥተጋብር የሚያጠነጥን ሀሳብ ነው፣ በሀገር እና በሕዝብ መካከል የጋራ ማንነት እና ትስስር ለመፍጠር፣ በማንነት፣ በሃይማኖት መካከል፣ በታሪክ እና በባሕል መካከል ሊኖር በሚችል ማንኛውም መስተጋብር አስተማማኝ መቀራረብ መፍጠር፣ በትውልድ ቅብብሎሽ የተቀበልነውን ታሪክ ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ጠንካራ ሀገር ማስረከብን የሚመለከት ነው ይላሉ።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጡ ሀገርን ለትውልድ ማብቃት ነው። ዓለም በደረሰበት ሥልጣኔ ባይታዋር ሳይኾኑ ቆሞ ላለመቅረት የሚደረግ ትግል፣ ከውስጥም ኾነ ከውጭ የሀገረ መንግሥትን ቀጣይነት የሚፈታተን አደጋ ባጋጠመ ጊዜ አደጋን መቀልበስ፣ በመስዋዕትነት ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ ሀገሩን የሚያስቀጥል ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ ነው ብለዋል።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ በዓለም አደባባይ ተሰሚነትን የማሳደግ እና የመጎናጸፍ ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። ድህነትን፣ ኋላቀርነትን እና በሽታን መፋለም፣ ራስን መቻል፣ በዓለም አደባባይ መኩራት፣ የማይቀለበስ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ጉዳይ እንደኾነ ነው የገለጹት። ብዝኃነት ባለባት ሀገር ሰውነትን መቀበል፣ ብዝኃነትን ማክበር፣ በሃይማኖት እና በማንነቶች መካከል የትብብር መንፈስን እና አብሮ የማደግ መንፈስን ማጎልበት፣ በማኅበረሰቡ ያሉ ባሕሎች፣ ወጎች፣ ልማዶች እና እሴቶች ተጠብቀው ዘመናዊነትን እንዲላበሱ የማድረግ ሂደትም ነው የሀገረ መንግሥት ግንባታ።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ ቀጣይነት እና ዋስትና እንዲኖረው በሕግ አስፈላጊነት ላይ መተማመን እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ቅቡልነት ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ችግር ሲያጋጥም ከገጠመው ችግር በቀላሉ መውጣት የሚያስችል ሀገራዊ አቅም መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

እንደ ሀገር በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ መግባባት፣ ጥቅሞች እንዲከበሩ እስከ መስዋዕትነት ድረስ ራስን ማዘጋጀት ነው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዳይ ይላሉ። በራሱ ላይ መከፋፈልን ያነገሰ ቤት አይቆምም የሚሉት ተመራማሪው ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው፣ ከተበታተኑበት ወጥተው ወደ አንድነት መጥተው ጥንካራ ሀገረ መንግሥት ያቆሙ ሀገራት መኖራቸውን ተናግረዋል።

በእርስ በእርስ ጦርነት ዋጋ የከፈለችው አሜሪካ የልዩነቷን ምንጭ ወደ አንድነት በማምጣት ጠንካራ ሀገር መሥርታለች፣ አሜሪካውያን ከልዩነት ወደ አንድነት የሚል መፈክርም አላቸው ይላሉ። የሃይማኖት ተቋማት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል። የሃይማኖት ተቋማት ማኅበራዊ ትስስርን በማጎልበት፣ የባሕል ጥበቃን በማሳደግ፣ የሕዝብ ተሳትፎ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ጉልህ ድርሻ አላቸው ነው የሚሉት።

ለማኅበረሰብ ተሳትፎ ማዕከል ኾነው እንደሚያገለግሉ እና ፍትሐዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። የሃይማኖት ተቋማት የጋራ እሴት፣ መቻቻል እና መተባበር እንዲጎላ፣ ግጭትን በመፍታት፣ እርቅን በማስፋፋት ሀገረ መንግሥት ጤናማ ኾኖ እንዲሄድ ያስችላሉ ነው ያሉት። ባሕል እና እሴት እንዲጠበቅም የማይተካ ሚና እንዳለቸው ገልጸዋል። አንድ የሚያደርግ ብሔራዊ ማንነት ለመገንባት እንደሚያስችሉም አንስተዋል።

ስለ ሰላም እና አብሮነት ግንዛቤ በማሳደግ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እና የሰብዓዊ መብትን በማስተዋወቅ ሚና አላቸው ነው ያሉት። በሥነ ምግባር የታነጸ መሪ እና ትውልድ እንዲኖር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። የሃይማኖት ተቋማት የትምህርት ምንጭ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ከቻይናውያን የምንወስደው ትምህርት አለ ያሉት ተመራማሪው ቻይናውያን ኅብረ ብሔራዊ ሀገርን እንገንባ ብለው ጠንካራ ሀገር መገንባታቸውን ገልጸዋል። ቻይና ውስጥ ብዝኃነት አለ፣ ከ56 በላይ ብሔረሰብ ይኖራል፣ 92 በመቶ የሚኾውን የያዘው ደግሞ ሀን የሚባለው አንድ ብሔር ነው፣ 8 በመቶውን የሚይዙት ደግሞ 55ቱ ናቸው ነው ያሉት።

ሌሎች እንዋጣለን ብለው ሳይሰጉ፣ ተከባብረው እና በሀገራቸው ኮርተው ይኖራሉ ነው ያሉት። በውስጣቸው በተፈጠሩት አንድነት ጠንካራ ሀገር መገንባታቸውን ነው የተናገሩት። ቻይና ዛሬ ከደረሰችበት ከመድረሷ በፊት የውድቀት ክፍለ ዘመን ብለው የሚጠሩት የውርደት ዘመን ነበራቸው፣ አቅም ስላልነበራቸው የተዋረዱበት፣ በቅኝ ገዢዎች የተዋረዱበትም ዘመን ነበራቸው።

ግዛቶቻቸውን ተነጥቀው፣ የወደብ ከተሞቻቸውም ተወስዶባቸው ነበር። የእርስ በእርስ ጦርነት ፈትኗቸዋል፣ ነገር ግን ለምን እንደዚህ ኾን ብለው ራሳቸውን ፈትሸው በመሥራታቸው ታላቅ ሀገር ገንብተዋል ነው ያሉት። ያጧቸውን ግዛቶች ወስደዋል ይላሉ። ቻይና እ.ኤ.አ በ1971 በተባበሩት መንግሥት ድርጅት መቀመጫ አልነበራትም። ዛሬ ላይ ግን ድምጻቸውን በድምጽ ከሚሽሩ አምስት ሀገራት መካከል ቻይና አንዷ ናት ነው ያሉት። መሪዎቻቸው ለሕዝብ ታማኝ ኾነው ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሠርተዋል፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ሲገነባ ችግር ሲገጥም እንኳን መልሶ መቋቋም ይቻላል ነው የሚሉት።

ቻይናውያን በሀገረ በቀል ዕውቀት እና በጠንካራ ሥነ ልቦና የተገነባ ሀገር መሥርተዋል። ኢትዮጵያውያንም ከእነርሱ የምንወስደው ትምህርት አለ ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ዕድል እና እርሾ አለን ይላሉ። ፈተናዎቻችን ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት አለብን ብለዋል። ጠንካራ መንግሥት ለመገንባት መግባባት ይገባል ብለዋል። የኢኮኖሚ ጸጋ አለን ግን ሳንጠቀመው በድህነት እንኖራለን፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ ስደት፣ ሞት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን ነው የተናገሩት።

የልዩነት ምንጭ በማይኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ የልሂቃን ልዩነት መኖር ፈተና መኾኑንም አንስተዋል። በባሕር ተጠቃሚነት እና በሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም አለባቸውም ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን ማምጣት እንደሚችሉም ተናግረዋል። ናይጀሪያ በእርስ በርስ ግጭት በነበረችበት ጊዜ የሃይማኖት ተቋማት ገብተው ሰላምን አምጥተዋል።

በኢትዮጵያም የሃይማኖት አባቶች ግጭትን በማስቆም ትልቅ ታሪክ አላቸው ይላሉ። ባሕላቸውን ተጠቅመው ግጭትን የሚያስቆሙ ሽማግሌዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። ኢትዮጵያውያን ጠንካራ የኾነውን ባሕላዊ ሽምግልና መጠቀም አለብን ነው ያሉት። ያጣነውን ሰላም ለመመለስ ርብርብ እናድርግ ያሉት ተመራማሪው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንድንገነባ፣ የጀመርናቸውን እንድጨርስ የሰላም አውድ እንዲኖር ማድረግ ይገባል ብለዋል። ሰላማዊ ውይይቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ተሻግራ ጠንካራ እንድትወጣ ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም፣ የመዳኛ ምስጢሩ መሰብሰብ፣ አንድነት ነው ብለዋል። ምርጫችን ሰላም፣ ምርጫችን ኢትዮጵያን ማስቀጠል፣ አንድነት ነው ይላሉ። ሰላምን ለመመለስ እና ሀገረ መንግሥትን ለማጠናከር የሃይማኖት ተቋማት ሚና ላቅ ያለ ነው ያሉት ተመራማሪው አኹን የገጠመን ችግር ከሃይማኖት አባቶች እና ከሃይማኖት ተቋማት በላይ አይደለም ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት መልካም እሴቶቻቸውን ተጠቅመው ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በባሕር ዳር ከተማ ለምለም ዘንባባዎች ውስጥ ሰላም ብቻ ነው የሚዘመረው” ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ
Next article“ሀገር በስስት እና በተስፋ የሚያያችሁ፤ የነገ ዕድላችን በእጃችሁ ላይ የወደቀው ወጣቶች የትውልዱ ዐይን እና ተስፋ በእንናት ላይ ነው” ፋሲል ታዬ