
ባሕርዳር: ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሁለተኛ ቀን ውሎውን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን ባሳተፈ መንገድ እየተካሄደ ነው። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችም “ሰላም ለሁሉም” እያሉ የዓደባባይ ሰልፍ እያደረጉ ወደ ኮንፈረንሱ ስታዲየም ገብተው እየተሳተፉ ነው።
በኮንፈረንሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ እንግዶች ስለሰላማችን ለመምከር ወደ ውቢቷ ከተማ እንኳን ደና መጣችሁ ብለዋል። ሰላም ወዳዱ የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ በጠዋቱ ከየአካባቢው ተሠባሥቦ በኮንፈረንሱ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ይህም ሕዝቡ ሰላምን አጥብቆ የሚሻ ለመኾኑ ማሳያ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ይሄንን የመሰለ የሰላም መድረክ በውቢቷ ከተማ በማካሄዳቸውም አመሥግነዋል። እንግዶች በከተማዋ ተገኝተው ሰላምን ከመስበክ በተጨማሪ የልማት እንቅስቃሴዋን በመመልከት ስለማበረታታቸውም ጠቅሰዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት በባሕር ዳር ከተማ ተገኝተው የሕዝቡን ኑሮ እና ልማት መመልከታቸው ከተማዋ እና ነዋሪዎች በከፋ የሰላም እጦት ውስጥ እንደሚኖሩ የሚናፈሰውን የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ የሰበረ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ምክትል ከንቲባው “በባሕር ዳር ከተማ ለምለም ዘንባባዎች ውስጥ ሰላም ብቻ ነው የሚዘመረው” ሲሉም ተናግረዋል። ይህ የሰላም ኮንፈረንስ በተሳካ መልኩ እንዲከናወን የበኩላቸውን የተወጡ አካላትን እና የባሕር ዳር ወጣቶችን በሙሉ ምክትል ከንቲባው አመሥግነዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን