
ደሴ: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር እየተሠራ የሚገኘው የሦስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ በጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስታውቋል። የከተማውን የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የኮምቦልቻ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የመንገድ ግንባታው በጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት መዘግየቱን አስታውሰዋል። ይሁንና የዞኑ አሥተዳደር ከክልሉ እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ ውይይት የጸጥታ ችግሩ ሳይበግረን ተቋራጩ ግንባታውን እንዲያከናውን አድርገናል ብለዋል።
የአስፋልት መንገዱ በኅብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብበት ነበር ያሉት አቶ አሊ የእግረኛ መንገድ፣ የመብራት እና ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል። የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ ዑስማን እንድሪስ በከተማዋ ውስጥ እየተሠራ የሚገኘው የአስፋልት መንገድ ሦስት ኪሎ ሜትር እርዝመት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 20 ሜትር ስፋት እንዳለው ተናግረዋል።
በእስካሁኑ የከተማ መንገድ የማስፋት ሥራ፣ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የድሬኔጅ ሥራዎች፣ ሰብ ቤዝ ንጣፍ፣ ቤዝ ኮርስ ንጣፍ እና የስትራክቸር ተግባራት ተከናውነዋል። የአስፋልት ንጣፍ ሥራው ወደ መጠናቀቁ እንደተቃረበ እና እስከ ሰኔ አጋማሽ ለማጠቃለል እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላኩ አያሌው ከተማ አሥተዳደሩ ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች እንዲገጠሙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፣ የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ እና የዞንና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እየተሠራ የሚገኘውን የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሂደት በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!