
ደሴ: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ በወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሂዷል። በውይይቱ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ የተገኙ የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎችም በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም አሁንም ግን ትንኮሳዎች ስላሉ መንግሥት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እና የተጀመሩ የአስፓልት መንገድ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። “መንግሥት እያከናወነ ያለውን ሰላም የማጽናት ሥራ እንደግፋለንም”ብለዋል።
“በከተማችን በኅብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው ለጽንፈኛ ኃይሉ መረጃ የሚያቀብሉ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ” ያሉት ነዋሪዎች እነዚህን ሰላም ጠል አካላትን መመንጠር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። መንግሥት በራሱ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የጽንፈኛ አጋሮች ስላሉ የራሱን መዋቅር ሊፈትሽ እንደሚገባም ገልጸዋል::
በሌላ በኩል ነዋሪዎቹ መንግሥት ሊፈታልን ይገባል ያሏቸውንም የልማት ጥያቄዎች አንስተዋል። በተለይም የመብራት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት፤ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተደራሽነት እና የፍትሐዊነት ጉድለት እና የሃይማኖት ተቋም የቦታ ጥያቄ ምላሽ መዘግየት በነዋሪዎቹ ከተነሡ የልማት ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር፣ የኑሮ ውድነት መባባስ፣ የትምህርት መቋረጥ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ የተዘጋው የመቅደላ አምባ መካነሰላም ዩኒቨርሲቲ ካምፓስም እንዲከፈት ጠይቀዋል። የመካነሰላም ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላኩ አያሌው የዩኒቨርሲቲው ጉዳይን እና የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ነው የተናገሩት። የዕምነት ቦታ ጥያቄን በተመለከተ በሰው ፍላጎት ሳይኾን በከተማው ፕላን መሠረት ጥያቄው እንደሚፈታ ነው ያስገነዘቡት።
የመብራት ሰብስቴሽን፣ የመንገድ፣ የውኃ እና የአስፓልት ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የጠቆሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር የውስጥ ለውስጥ መንገድ እየተሠራ ነው ብለዋል። የፍትሐዊነት ጥያቄዎችን በትኩረት እንደሚፈትሹም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን “የቅሬታ መፍቻ ሰላማዊ ንግግር እንጅ መሳሪያ ማንሳት አይደለም” ብለዋል።
“ሕዝቡ ሰላም ጠምቶታል ዋነኛ የሰላም ባለቤት እና ጠባቂው ደግሞ ሕዝቡ ነው” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው “ሥልጣን የሚገኘው በኀይል ሳይኾን በሕዝብ ድምጽ ብቻ በመኾኑ የጽንፈኞችን አካሄድ ሕዝቡ በቃ ማለት እና መታገል ይኖርበታል” ነው ያሉት ።
በሰላም እጦት ብዙ ኪሳራ እየደረሰ በመኾኑ ለሕግ ማስከበር ሥራው ሕዝቡ ተባባሪ መኾን እንጅ ጽንፈኞችን መደበቅ እና መረጃ ማቀበል ስቃይ ከማራዘም ውጭ መፍትሄ እንደማያመጣ መገንዘብ ይገባዋል ብለዋል። በመኾኑም ከመንግሥት ጎን መቆም አለባችሁ ነው ያሉት።
አሁናዊ የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ያሉት አቶ አሊ እንደ ዞን ከሚያዝያ ወር ወዲህ ብቻ ከ600 በላይ ታጣቂዎች የመንግሥት እና የሕዝብን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገብተዋል ነው ያሉት ። ነዋሪዎች ከተማችሁን በንቃት ጠብቁ፣ ተደራጅታችሁ ፀጉረ ልውጦችን መንጥሩ፣ የቀበሌ መሪዎችን በማጠናከር አግዙ ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የልማት ጥያቄዎችን መንግሥት ደረጃ በደረጃ ይመልሳል ብለዋል።
የመብራት ሰብስቴሽን ግንባታ ይከናወናል፣ የውኃ ጥያቄን ለመመለስም ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ ቁፋሮው ተጠናቅቋል፤ የመስመር ዝርጋታውም ይከናወናልነው ያሉት። የአስፓልት መንገድ ግንባታም ከክልሉ እና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር እየሠሩ እንደኾነ እና ሥራው ከክረምት በፊት እንደሚጠናቀቅ አቶ አሊ አብራርተዋል።
የተዘጋው የዩኒቨርሲቲ ካምፓስም ሊከፈት የሚችለው ሕዝቡ ለአስተማማኝ ሰላም መስፈን ሲተባበር ነው ብለዋል። የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ሕዝቡን ለመጠበቅ እንደኾነም ነው የተናገሩት። በመኾኑም ሕዝቡ ሠራዊቱን ሊያግዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከማኅበረሰቡ ለጽንፈኞች መረጃ የምትሰጡ ተመከሩ ከድርጊታችሁ ታቀቡ ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ዘውዱ ሰጣርጌ ልማት መጠየቅ መብት ነው፤ ነገር ግን ልማት እንዳይሠራእንቅፋት የኾኑትን በቃ ማለት ግን ይገባል ነው ያሉት። ለሰላም ሁላችንም በጋራ መሥራት አለብንም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን