ነጻ፣ ገለልተኛ እና ዘመኑን የሚመጥን ሪፎርም ተግባራዊ እንዲኾን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

7

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን በመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ዙሪያ ከክልል መሪዎች እና ዳይሬክተሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም በክልሉ በመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ጉዞ ውስጥ የተቋማትን ዘላቂነት ለማጽናት እና የመንግሥትን የማሥፈጸም አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ሪፎርሙ በክልሉ ብሎም እንደ ሀገር የተከሰተውን የኢኮኖሚ ችግር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮችን የሚቀርፍ መኾኑንም ገልጸዋል። በክልሉ ዘላቂ ልማትን እና ሳይንሳዊ እውቀቶችን ከሀገራዊ እሴቶች ጋር አጣጥሞ ለማዝለቅ የሚያግዝ እንደኾነም ተናግረዋል።

የሠራተኛውን አቅም እና ሥነ ምግባር በማሻሻል አገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን ፋይዳው የጎላ መኾኑን ነው የተናገሩት። በሙያ ምደባ፣ በሥራ ምዝና፣ በክፍያ ሥርዓት እና በመረጃ ሥርዓት ይታይ የነበረውን ችግር ለመፍታት ያግዛልም ብለዋል።

የክልሉን የመንግሥት ተቋማት አደረጃጀት ከፌዴራል ተቋማት አደረጃጀት ጋር እንዲናበብ ትኩረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት። ክልሉ የመንግሥት ተቋማትን እና አሥተዳደርን በማሻሻል ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችአምላክ ገብረማርያም የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ሰፊ ሥራ የተከናወነበት መኾኑን አንስተዋል። ተቋሙን ለማዘመን፣ ለሚሰጠው አገልግሎት ደግሞ በቂ ክፍያ ያለው፣ ተጠያቂነትንም የሚያረጋገጥ ሥርዓት ለመገንባት በየጊዜው ሪፎርም ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። ክልሉም ሪፎርሙን ለመተግበር አዋጅ እና ደንቦችን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ኮሚሽነራ እንዳሉት ሪፎርሙ ዘላቂነት ያለው፣ ውጤታማ የኾነ የድጅታላይዜሽን ሥራ ለመዘርጋት፣ በሥነ ምግባር እና በእውቀት ሊመራ የሚችል መሪ እና ባለሙያ ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የታቀዱ ክልላዊ የልማት ግቦችን የሚያሳካ፣ የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት የሚያረካ፣ የመንግሥትን አገልግሎት እና አሥተዳደር ሥርዓት የሚፈጥር መኾኑንም ነው የገለጹት። የክልል ተቋማት አደረጃጀት በየደረጀው ካለው የፌዴራል ተቋማት ጋር ተናባቢ እንዲኾን ያደርጋል ነው ያሉት።

የክልሉ ተቋማት አደረጃጀት የአካባቢውን የመልማት አቅም እና የሕዝብ ብዛት መሠረት ያደርጋልም ብለዋል። የተቋማትን ተግባር እና የኀላፊነት ሚና የሚለይ፣ ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንጻር ተጠሪነታቸውን ጠብቀው እንዲደራጁ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ሪፎርሙ ውጤታማ የሚኾነው ሁሉም ባለቤት ኾኖ መሥራት ሲችል መኾኑንም ተናግረዋል።

ተሳታፊዎችም ተቋማት በቴክኖሎጅ የተደገፈ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ አንስተዋል። ሪፎርሙ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል መኾን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የሀገር ተስፋ ከኾኑ ወጣቶች ጋር በጋራ መትጋት የሀገር ብልጽግናን ያረጋግጣል” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next articleመንግሥት እያከናወነ ያለውን ሰላም የማጽናት ሥራ እንደሚደግፋ የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።