
አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ጋር በየደረጃው ሲካሄድ የነበረው ውይይት በማጠቃለያ መድረክ ተጠናቅቋል። “የወጣቶች ሚና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው መድረክ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች እና ከየክፍለ ከተማው የተወከሉ ወጣቶች ታድመዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከተማዋ ላይ እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና መሰል ፕሮጀክቶች ሰው ተኮር እና የከተማዋን ገጽታ የሚገነቡ ናቸው ብለዋል። በመኾኑም በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አንስተዋል። ለእነዚህ ተግባራትም የከተማ አሥተዳደሩን መሪዎች አመሥግነዋል።
በቀጣይም በልማት ተግባራት በመሳተፍ እና የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ የከተማዋ ዋልታ መኾናቸውን እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል። በቀጣይ በትኩረት ቢሠሩ እና ተጠናክረው ቢቀጥሉ ያሏቸውን ሃሳቦችንም አንስተዋል።
ካነሱት አንኳር ነጥቦች መካከል፦
👉 የሥራ ዕድል ፈጠራን ማበረታታት እና የሥራ ፈጠራን በተመለከተ ተከታታይ ግንዛቤ መፍጠር
👉 የተዘዋዋሪ ብድርን በመፍቀድ የሥራ ዕድልን ማስፋት
👉 ወጣቶች ዕውቀት እና ክህሎት እንዳላቸው ታውቆ የፋይናንስ ችግርን ብድሮችን በማመቻቸት መቅረፍ
👉 የሱስ ማገገሚያ ቦታዎችን አብዝቶ መገንባት እና ወጣቶችን መታደግ
👉 ተቋማዊ አሠራር ተቀርጾ የወጣቶች የቤት ባለቤትነትን ማረጋገጥ
👉 የስፖርት ማዘውተሪያዎች ክፍት ኾነው ወጣቶች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ እና መሰል ጉዳዮችን አንስተዋል።
ለተነሱ ጥያቄዎች ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ምላሽ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በዚህ በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ከ310 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ያም ቢኾን ካለው የሥራ አጥ ቁጥር አንጻር በቂ አይደለም ነው ያሉት ከንቲባዋ።
በቀጣይ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ሁሉ አቀፍ መፍትሄ ለማምጣት ይሠራል ብለዋል። የወጣቶች የቤት ጥያቄን በተመለከተ በቀጣይ እንደከተማ አሥተዳደር የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት። ከንቲባ አዳነች የወጣቶች ጥያቄም ደረጃ በደረጃ ይመለሳል ብለዋል።
ወጣቶች በቁጠባ ሂደት በማለፍ በአማራጮች መጠቀም እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ሌሎች የተነሱ ጥያቄዎችን በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በየደረጃው እንደሚፈቱም አረጋግጠዋል።
የሀገር ተስፋ ኩራት እና ጉልበት የኾነው የወጣት ኃይል በሀገሩ ጉዳይ በያገባኛል መንፈስ እና በቁርጠኝነት በመሥራት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መትጋት ይገባዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን