
አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አስመልክቶ ከኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለፌዴራል ተቋማት በምክር ቤቱ የተመደበን የመንግሥት በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል እና ተቋማት ከኦዲት ግኝት ነጻ እንዲኾኑ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ይሠራል።
የበጀት ዓመቱን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ.ር) ቋሚ ኮሚቴው ለፌደራል ተቋማት የተሠጣቸው በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን በውይይት እና በመሥክ ምልከታ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረጉን አንስተዋል።
በመንግሥት የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እና ግብ እንዲውል በተደረገው ክትትል እና ቁጥጥር ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ሰብሳቢዋ አንስተዋል።
የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው ተቋማት አሠራሩ በሚፈቅደው ደንብ እና መመሪያ መሠረት የእርምት እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ገልጸዋል።
በቀጣይ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተመደበው በጀት የሀገሪቱን ፖሊሲዎች፣ ሕጎች እና አሠራሮችን ተከትሎ ለተቀመጠለት ዓላማ እና ግብ እንዲውል ሁሉም የኦዲት ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የኦዲት ባለድርሻ አካላትም የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በኦዲት ግኝት ክትትል እና ቁጥጥር ሂደት የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር እያከናወኑት ያለው ሥራ የሚበረታታ እና ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮ የሚኾን ነው ተብሏል።
ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን