
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ” ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል። የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባል እንዲሁም የኮንፈረንሱ ዝግጅት ሰብሳቢ መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከአማራ ክልል መንግሥት እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ኮንፈረንሱን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አማካኝነት ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ እና በጅማ ተካሂዷል ብለዋል። በሰላም ኮንፈረንሶቹ ላይ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሃይማኖት ተቋማት በሰላም አስተምህሮ እና በግጭት አፈታት ዙሪያ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማጠናከርም አስፈላጊነቱን አንስተዋል።
በኅብረተሰቡ ዘንድ የሰላም ውይይቶችን ለማስፋት፣ የነበረውን የተጋመደ ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎለብት በማድረግ፣ ለበርካታ ዘመናት ሲጠቀምባቸው የነበሩትን መልካም እሴቶች ወደ ኋላ ቆም ብሎ በማሰብ አሁን እየታየ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ትምህርት ለመስጠት እና መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ ስሟ ከፍ ብሎ የሚታወቅ እና ዛሬም ድረስ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት ኾና የምትጠራ ናት ያሉት መልአከ ብርሃን ፍስሐ ለውጭ ወራሪም ተንበርክካ የማታውቅ ሀገር ናት ብለዋል። ለዚህ ያበቋት ደግሞ በሕዝቦቿ የተሰናሰለ የአንድነት ገመድ እንደነበር በዓለም የሚገኙ ታሪክ ጸሐፊዎች ዘግበው ያስቀመጡት እውነታ መኾኑን ነው የተናገሩት። 1888 ዓ.ም የዓድዋ ጦርነት ሕያው ምስክራችን ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ተብሎ በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍት ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢትዮጵያ ከሕገ ኦሪት ጀምራ ፈጣሪዋን የምታመልክ፤ ሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይ፤ በእምነት፣ በቀለም፣ በጎሳ የማይለያዩ፣ በሕዝቦቿ አብሮነት እና የተባበረ ክንድ ታፍራ እና ተከብራ የምትኖር ታላቅ ስመ ገናና ሉዓላዊት ሀገር ነበረች ነው ያሉት። ይህ መልካም ዝናዋ በዓለም ድርሳናት ተመዝግቦ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከፍታ እንዲቀጥል የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘውት እንደነበር አንስተዋል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው የእርስ በርስ ግጭት የብዙ ሰዎችን ሕይዎት ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል፣ ሕዝቦች ተወልደው በአደጉበት ቀያቸው እንዳይኖሩ ኾነዋል ነው ያሉት። ለስደትም ተዳርገዋል፣ የኢትዮጵያን ዝናም ዝቅ አድርጎታል ብለዋል።
አሁን አሁን እየኾነ ያለው ግጭት ሲታይ የሃይማኖት ተቋማት እያሉ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሳይጠፉ፣ ሰላምን ለማስፈን ባለድርሻ አካላት መኖራቸው እየታወቀ ለምን ድርጊቱ አይቆምም?የሚለው በእያንዳንዳችን ልቡና በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።
ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ የተዘጋጀው ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ግርማ ሞገሳቸውን ተጎናጽፈው፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመኾን እየታየ ያለው የእርስ በርስ ግጭት በዘላቂነት እንዲቆም እና ሰላም እንዲሰፍን፣ ወደ ነበረው አብሮነታችን እንድንመለስ፣ አብዝቶ በማስተማር ድርሻችን እንዲንወጣ ለማድረግ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን