
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል። በኮንፈረንሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሰላም ኮንፈረንስ በአማራ ክልል መካሄዱ ለአማራ ክልል ሕዝብ ትርጉሙ ትልቅ ነው ብለዋል። ኮንፈረንሱ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮነት የሚመከርበት እና ሰላም ሥር እንዲሰድ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ዋና ዓላማቸው የሰው ልጅ እና ፈጣሪን ማገናኘት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በዓለማዊ ሕይዎቱም የተቃና እንዲኾንም አስተዋጽኦ አላቸው ነው ያሉት። የሰው ልጅ ሁልጊዜ መቻቻልን እና ሰላምን ላይፈጥር ይችላል፣ በመቻቻል እና በሰላም እንዲኖር የሚያደርጉት በውስጣችን ያሉት እሴቶች ናቸው ብለዋል። እሴቶች የሚገኙት ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት ነው፣ የሃይማኖት ተቋማት በሕዝብ መካከል ትስስር እንዲኖር፣ የሕዝብ እና የመንግሥት ግንኙነት ጤናማ እንዲኾን ያደርጋሉ ነው ያሉት።
አሁን ላይ የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት ተዛብቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰው እና ተፈጥሮ ተስማምቶ የሚገናኝባቸው የሃይማኖት ተቋማት መኾናቸውንም ገልጸዋል። የጋራ አንድነት እንዲጸና፣ የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ ኮንፈረንሱ ትልቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል። ከንግግር ባለፈ በተግባር እና በአኗኗር ሰላማዊ መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል። በኮንፈረንሱ የሚነሱ ጉዳዮች ውጭ ላይ ወጥተው በኅብረተሰቡ ዘንድ ጠቃሚ እንዲኾኑ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ኮንፈረንሱ ፍሬያማ የሚኾነው በአዳራሽ የተወሰነው ውሳኔ፣ የተመከረው ምክር በሕዝቡ ዘንድ ደርሶ በተግባር ሲኖር ነው ብለዋል። በኩራት የምንናገራቸው በጎ ታሪክ አሉን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከበጎ ታሪኮች በተጓዳኝ መታረም ያለበት የግጭት አዙሪትም የታሪካችን አንድ አካል ነው ብለዋል። ግጭቱ ደግሞ ድህነትን እየመገበ ሀገርን መጉዳቱን ተናግረዋል።
ግጭትን ማቆም እንችላለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከትልቅነት ያወረዱንን ግጭት እና ደህንትን መታገል እና ማረም ይገባናል ነው ያሉት። የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ይሄን ለማረም ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
ሃይማኖቶች የውስጥ ችግራቸውን መፍታት፣ እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ማስተካከል እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሚዛኑን የጠበቀ የመንግሥት እና የሕዝብ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል። የጋራ የኾነውን ሕዝብ ለመጥቀም መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ሰላምን ለማጽናት መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና ሌሎች ልዩነቶችን የአብሮነት ምንጭ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን ከማጽናት እና አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር ለሀገር ዕድገት እና ለልማት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አመላክተዋል። መልካም አሥተዳደር እንዲሰፍን እና ግብረ ገብነት እንዲሰፍን ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት። የሰውን ሃብት የሚጸየፍ፣ አምላኩን የሚፈራ፣ ሰውን የሚያከብር ትውልድ እንዲፈጠር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የተዛቡ ግንኙነቶችን ማደስ እና በአንድነት መሥራት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። “የአማራ ክልል መሪዎች እና ሕዝብ የሰላምን ፋይዳ የምናውቀው በንድፈ ሃሳብ ሳይኾን አጥተናት ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላም ኮንፈረንሱን በአማራ ክልል ማዘጋጀት ልዩ ትርጉም ስለነበረው በደስታ ተቀብለን በአጭር ጊዜ አዘጋጅተናል ነው ያሉት። ኮንፈረንሱ የሰመረ እንዲኾን ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ለሀገራችን አንድነት እና ለሕዝባችን አብሮነት ይህን አደረግን የምንልበት ጉባኤ እንዲኾን እመኛለሁም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን