
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ጣናን ተንተርሳ፣ ዓባይን መቀነቷ አድርጋ እና በዘንባባዎቿ በተሞሸረችው ባሕር ዳር ከተማ እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ አካባቢ እንደተመሠረተች ይነገርላታል ነው ያሉት። ከተማዋ ለብዙ ዓመታት የተለያዩ ሃይማኖቶች ተቻችለው እና ተከባብረው የኖሩባት ከተማ እንደኾነችም ተናግረዋል ምክትል ከንቲባው። ነዋሪዎቿ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት እና በሌሎች ዘርፎች ተከባብረው፣ ተቻችለው እና ተዋድደው የኖሩባት ምሳሌ ከተማ ስለመኾኗም ተናግረዋል። ሰላም ማኅበራዊ እሴት ነው ያሉት አቶ አስሜ ሰላም ለፍጥረታት ሁሉ እጅግ መሠረታዊ የኾነ ነገር ነው ብለዋል።
ሰላም የሰው ልጅ ለኾነ ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባ፤ ለሁለንተናዊ ሕይዎት መሠረት የኾነ ጉዳይ እንደኾነ ነው የገለጹት። “ስለ ሰላም መስበክ፣ ስለሰላም መዘከር የሁልጊዜም ተግባር ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት። የሰላም መታጣት የሚያመጣውን ጣጣ ማስገንዘብም ያስፈልጋል ብለዋል ምክትል ከንቲባው።
የሃይማኖት ተቋማት የቆሙለት ዋናው መሠረታዊ ነገር ዓለማዊ ፍላጎት እንዳልኾነም ተናግረዋል። ይልቁንም የሃይማኖት ተቋማት የቆሙለት ዋና ዓላማ ለሰላም መስፈን በርትቶ መሥራት እና ከሀገር አልፎ በዓለምም ጭምር ሰላም እንዲመጣ መጸለይ ነው ብለዋል።
የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተኳረፉትን ማቀራረብ ዋና ተግባራቸው እንደኾነም አንስተዋል። በማኅበረሰቡ መካከል ያልተጣጣሙ ፍላጎቶች ሲያጋጥሙ፤ ከማኅበረሰቡ ባሕል እና ወግ ባፈነገጠ መንገድ ግጭት ያጋጥማል ነው ያሉት። በዚህ ጊዜ ሰብዓዊ ፍጡር ይሞታል፣ ንብረት ይወድማል ብለዋል። እድገት እና ልማት ይገታል ነው ያሉት።
ከተማችን ባሕር ዳር ሰላም በደፈረሰ ሰዓት ምን ያህል ዋጋ እንደሚከፈል በተግባር አይታለች ነው ያሉት። ይሁንና ያጋጠማትን ችግር በጠንካራ መሪዎች፣ በብርቱ የጸጥታ አካላት እና በሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ አማካኝነት ያን ጊዜ አልፈን እዚህ ደርሰናል ብለዋል አቶ አስሜ።
ሰላም በደፈረሰ ጊዜ ማኅበራዊ መስተጋብር ሲደፈርስ በተግባር አይተናል ነው ያሉት። አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ እና የተጀማመሩ የልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን