
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሦስተኛው የሃይማኖት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበር እና ለአብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኮንፈረንሱ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የአማኞች ሀገር እንደኾነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ የሃይማኖት አባት ቃል እና ተግሳጽ ይከበርባታል። ለሺህ ዘመናት በዘለቀው ታሪኳ ሃይማኖቶች እና የሃይማኖት አባቶች ሚና ላቅ ያለ ነበር። የሃይማኖት አባቶች በታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየመከሩ፣ እየዘከሩ፣ አንድነትን እየሰበኩ ለታላቅ ሀገር የተገባውን ሲያደርጉ ኖረዋል። ነፍስ እና ስጋን የሚያሳታርቁት፣ የሰማይ እና የምድርን ምስጢራት የሚያራቅቁት የሃይማኖት አባቶች ለሰላም፣ ለአብሮነት፣ ለአንድነት እና ለጸና ኢትዮጵያዊነት ሚናቸው የላቀ ነው።
የሃይማኖት አባቶች ክፉን ነገር እያወገዙ፣ መልካም ነገርን እያስተማሩ፣ የተጣላን እያስታረቁ፣ አንድነትን እያደረጁ ኢትዮጵያን ሲገነቡ ኖረዋል። ዛሬም የኢትዮጵያ ተስፋዎች ናቸው። ዛሬም ለኢትዮጵያውያን አድባሮች ናቸው።
እንደ አድባር የሚቆጠሩ የሃይማኖት አባቶች ሰላምን እየሰበኩ፣ ጥልና ጥላቻን እያወገዙ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉና። ዛሬ በባሕር ዳር የተጀመረው ኮንፈረንስም ለሀገር ሰላም፣ ለመከባበር፣ ለአብሮነት እና ለአንድነት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!