ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ የባሕር ዳር አሥተዳደር ገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት መዋቅር አመራሮች እና ቡድን መሪዎች ጋር በመንግሥት አገልግሎት እና ስታንዳርድ ሪፎርም አተገባበር ላይ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን የሪፎርም ድጋፍ እና ክትትል ዳይሬክተር እንዳላማው ይታይህ የመንግሥት ሠራተኞችን ብቁ ለማድረግ ከሚተገበሩት መካከል አንዱ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደርን ለማሳደግ መኾኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል አንደኛው መንገድ በዲጂታላይዝድ መንገድ የአገልግሎት ተደራሽነትን እና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ መኾኑንም አንስተዋል። የንቅናቄው ዓላማ ሠራተኞችን በመንግሥታዊ አሥተዳደር ሪፎርም ላይ እውቅና ኖሮት በባለቤትነት እና በውጤታማነት እንዲሠራ ለማድረግ መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም ሪፎርሞች መደረጋቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው በተመረጡ ተቋማት እየተሞከረ የሚሰፋ መኾኑን ተናግረዋል። የሠራተኞችን ቁጥር ከመጨመር ብቃት ማሳደግ ላይ ማተኮሩም ሌላው ልዩ የሚያደርገው መኾኑን አክለዋል። አደረጃጀት የመቀየር ሳይኾን መረጃን እና አገልግሎትን ዲጂታል የማድረግ መኾኑንም አክለዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ አቅጣጫ ተሰጥቶበት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው የአመራሩን መረጃ እስከ ሰኔ መጨረሻ ለማጠናቀቅ መታሰቡንም ገልጸዋል።ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ያለውን ጉዳት የዘረዘሩት አቶ እንዳላማው ለማጣራት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የሪፎርሙ የመጨረሻ ግቡ የተቋምን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሳድግ ስለኾነ ከእያንዳንዱ ተቋም እና ሰው የሚጠበቅ ሚና ቢኖርም የጋራ ውጤቱ የኅብረተሰቡ ርካታ ስለኾነ ሁሉም በየሥራ ድርሻው መረባረብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ጤናው ምኅረቱ ሪፎርሙ የነበሩ ችግሮች እና ተቋማትን እንዲሁም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመለየት ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር 28 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና 6 ሺህ 500 ሠራተኞች መኖራቸውን የጠቀሱት መምሪያ ኀላፊው የኅብረተሰቡ ርካታ አነስተኛ መኾኑን አንስተዋል። በመፍትሄነትም ሠራተኛውን ማብቃት እና ለአገልጋይነት ማነሳሳት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አደረጃጀቱን ማመጣጠን እና ዲጂታላይዜሽንን መጠቀምም ተጓዳኝ ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ሪፎርሙ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ መዋቅሮች በተመሳሳይ ሂደት እንዲያልፉ ይፈለጋል። በመኾኑንም በከተማው በተመረጡ ተቋማት ለመተግበር ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ሠራተኞች አሠራሩ በቅንነት እንደሚቀበሉት ይጠበቃል ብለዋል።የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የመንግሥት አገልግሎት እና ሪፎርም በሀገር ደረጃ ከተጀመረ መቆየቱን ገልጸው በባሕር ዳር ከተማም ዛሬ ተጀምሯል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የመንግሥት ሠራተኞች እሳቤ አሁን ላይ ሀገሪቱ እና ክልላችን ከሚፈለገው የልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ሲታይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ መስተካከል ያለባቸው እሳቤዎች እና አሠራሮች መኖራቸውን አንስተዋል።የኅብረተሰቡን ርካታ ለማሳደግ ከሠራተኞች ጋር በመወያየት መግባባት እና ለተሻለ አገልግሎት መትጋት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይን ርካታ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።የተግባራት ዝግጅት፣ የተግባር እና የማጽናት ምዕራፍ እንደተከፋፈሉ ገልጸው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደራቸውም ሪፎርሙን ለመተግበር ቁርጠኛ መኾኑን አቶ አስሜ ገልጸዋል። ሠራተኞች ሪፎርሙን የኔ ብለው እንዲይዙት እና በእምነት እንዲተገብሩት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየግብረ ገብነት ግንባታ ድርሻው የማን ነው?
Next articleሦስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።