
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የትግራይ ሕዝብ ነጻነቱን ለማግኘት የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡
የትግራይና የአማራ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ ቤተሰባዊ ትስስር እና አንድነት ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን፣ በረጅሙ ታሪክ ውስጥም ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የሕዝብ ግጭት ኖሮ እንደማያውቅ አብን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡፡ ይሁን እንጂ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የቀረጸውን ፖሊሲ የፖለቲካ ፕሮግራሙ አድርጎ የተቀበለው እና የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ የዘለቀው ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) ብሎ የሚጠራው ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ባደረሰው ጥፋት እና ስርዓት ሰራሽ ጥቃት ምክንያት ግንኙነታቸው ፈተና ላይ ወድቆ መቆዬቱን አስታውቋል፡፡
ሕወሃት አሁንም በትግራይ ሕዝብ መካከል መሽጎ የጥፋት እና የሴራ መረቡን በመዘርጋት በርካታ ጥቃቶችን እና ውድመቶችን ማስከተሉንና በመላ አገሪቱ ላይ አንሰራፍቶት የነበረውን የአፈና ስርዓት ጠቅልሎ በትግራይ ሕዝብ ላይ አስፍኖበት እንደሚገኝ አብን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በትግራይ ሕዝብ እና በትሕነግ ቡድን መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ በመግለጽም ትሕነግ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ትግል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ በአማራ ሕዝብ ላይ ላደረሳቸው ህልቆ መሳፍርት በደሎች እና ስርዓት ሰራሽ ጥቃቶች ኃላፊነቱ የሕወሃት እንጅ የጨዋው እና የተከበረው የትግራይ ሕዝብ አለመሆኑን አብን፣ የአማራ ሕዝብ እና አገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደሚውቁት ንቅናቄው አስታውቋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ራሱን በመንደር እና በጎጥ አደራጅቶ እያጠቃው ካለው የትሕነግ አገዛዝ ጋር የሚያደርገውን ትግል አብን፣ የአማራ ሕዝብ እና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ሕዝቡ እንዲውቅም ንቅናቄው አመላክቷል፡፡ ሕዝቡ ነጻነቱን ለማግኘት የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልም አብን ጥሪ አቅርቧል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት መካከል ደንቃራ የሆነውን የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን ከራሱ ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ጋር በአንድነት ለመቆም፤ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት በሚያደርገው ትግል አብን ከጎኑ እንደሚቆምም በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ከሕወሃት መወገድ በኋላ የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ የቀደመውን ቤተሰባዊ ትስስራቸውን ወደ ነበረበት የሚመልሱበትና ሕዝባዊ አንድነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሚሆንም ነው ንቅናቄው የገለጸው፡፡
የአማራ ሕዝብ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ፈታኝ ወቅት ወገናቸው የትግራይ ሕዝብ ከሕወሃት ዘረኛ፣ ጠባብ፣ ጎጠኛ እና አፋኝ ስርዓት ነፃ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል በማገዝ እንዲቆሙ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥሪ አስተላልፏል፡፡