የግብረ ገብነት ግንባታ ድርሻው የማን ነው?

13

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቤተሰብ የመንግሥት፣ የትምህርት ተቋማት እና የቤተ እምነቶች ግብረ ገባዊ እሴቶችን እና ሕግጋትን በመቅረጽ፣ በማክበር፣ በማስከበር፣ በማሳወቅ እና በማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ማኅበራዊ ተቋሞች ናቸው።

በተለይም ደግሞ ሃይማኖታዊ ተቋማት ግብረገብነትን ለሃይማኖታዊ ግባቸው ስለሚጠቀሙበት ዋነኛ ግብረ ገባዊ ተቋማት ተደርገው ይወሰዳሉ። በሰዎች መካከል መረዳዳት እና መከባበር፣ መተዛዘን እና መተጋገዝ እንዲኖር፤ ደግነት እና ርህራሄ እንዲሰፍን የሚያደርጉም ናቸው፡፡

ይህ ጥረት በሌላ ገጹ ሲታይ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ሌብነት፣ ዝርፍያ፣ ውሸት፣ ተንኮል፣ የሰው ሕይዎት ማጥፋት እና የመሳሰሉት እኩይ ድርጊቶችን እንዲጠየፉ መጣር ይኾናል። ባጭሩ የአብዛኞዎቹ ቤተ እምነቶች ሥራ የሰው ልጅ በመንፈሳዊ ሕይዎቱ ዘለዓለማዊነትን፣ በምድራዊ ሕይዎቱ ደግሞ ሰላም እና ፍቅርን እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ልክ እንደ ግብረገብነት የሃይማኖቶች ዋና ዓላማ እኩይ ነገሮችን ማስወገድ እና ሰናይ ነገሮችን ማጎልበት ስለኾነ ማለት ነው።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል መምህር መልዓከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን እንዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘመናዊ ትምህርት አሁን ከደረሰበት ሳይደርስ ብራና በመቅረጽ ለትውልዱ በአደረጃጀት ግብረ ገባዊ ትምህርትን ጭምር በተለያዩ መንገዶች ስታስተምር ቆይታለች ብለዋል። አሁን ላይም እያስተማረች ትገኛለች ነው ያሉት። በዚህም ትውልድን በመቅረጽ እና በማነጽ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ትውልዱ ሥርቆትን፣ ዝርፊያን፣ ግድያን እንዲጸየፍ፣ እናት አባቱን ብሎም በሰው ልጆች መካከል መከባበር እንዲኖር ሠርታለች ነው ያሉት። ሩህሩህነት፣ በጎነት፣ መተጋገዝ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለትውልዱ አሥተምራለች፤ እያስተማረችም ትገኛለች ብለዋል።

ይሁን እንጅ አሁን ላይ በውጫዊ እና ውስጣዊ ተጽዕኖዎች ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ ማጭበርበር፣ ዘረፋ፣ ግድያ፣ ሥርቆት ፈተና እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በቀጣይ የሃይማኖት ተቋማት በተደራጀ መንገድ ማስተማር፣ አማኙም በቤተ እምነቶች ተገኝቶ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን መማር እና መተገብር ይገባል ብለዋል።

ልጆች በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ወላጆች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። መንግሥትም መልካም አሥተዳደርን ማስፈን፣ በትምህርት ተቋማት ደግሞ የሥነ ምግባር ትምህርቶች እንዲሠጡ የማድረግ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። ሚዲያዎች ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለው እንዲሠሩ፣ ከሕግ ውጭ የሚወጡ እና ትውልድን ወዳልተፈለገ ነገር የሚወስዱትን ደግሞ ተከታትሎ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋ እና ትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም በሰዎች መካከል መረዳዳት፣ መከባበር፣ መተጋገዝ እንዲኖር እና ደግነት እንዲጎለብት የሃይማኖቱ ትኩረት ነው ብለዋል። አሥተምህሮው ለሰዎች ብቻ ሳይኾን ለእንስሳት ጭምር መተግበር እንደሚገባ ሃይማኖቱ እንደሚያዝዝ ገልጸዋል። ፈጣሪ ያስቀመጣቸውን ትዕዛዛት ቅዱስ በመኾናቸው ትዕዛዛቱን በማክበር መተግበር ይገባልም ብለዋል።

በእስልምና ሃይማኖት ግብረ ገባዊ እሴትን ለማጎልበት መርሐ ግብር በማዘጋጀት በመስጅድ፣ እንደ ሠርግ፣ ለቅሶ፣ እድር በመሳሰሉ ማኅበራዊ ሁነቶች እና በጁምዓ ነባራዊ ሁኔታውን መሠረት ያደረገ ትምህርት ይሰጣል ነው ያሉት።

ኀላፊው እንዳሉት ግብረ ገባዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ ከተፈለገ የሃይማኖት አባቶች ትኩረታቸው ሃይማኖታዊ አሥተምሮው ላይ በማተኮር ሕዝብን የማቀራረብ ሥራ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል። መደማመጥ እና መከባበር ደግሞ መርህ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ደግሞ ለአባቶች ክብር ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎችን ሁሉ ከመበቀል ወጥቶ የመረጃውን ትክክለኛነት ማጥራት፣ መመርመር ይገባል ብለዋል። መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ቤተሰብም ልጆቹ በግብረ ገብነት ተቃኝተው እንዲያድጉ ትልቁን ድርሻ ወስዶ መሥራት እንዳለበት መክረዋል።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሠራ ነው።
Next articleለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ የባሕር ዳር አሥተዳደር ገለጸ።