
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፌደራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴን ጨምሮ፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ የፌዴራል ፖሊስ መኮንኖች እና ሌሎች ተገኝተዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ያለምዛፍ ጥላሁን በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት የጸጥታ ኀይሉን በማደራጀት መሠራቱን ገልጸዋል።በዞኑ ውስጥ በታጣቂ ቡድኑ ተይዘው የነበሩ ወረዳዎችን ከቡድኑ በማስለቀቅ ቀበሌዎችን ነጻ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በዞኑ በርካታ ቀበሌዎች ከታጣቂዎቹ ነጻ መኾናቸውንም አንስተዋል።
የታጣቂ ቡድኑ አቅም እየደከመ እና እየሸሸ ነው ያሉት አዛዡ ቡድኑን በማጽዳት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ብለዋል። ሕዝቡን ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በማቀናጀት አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ይሠራል ነው ያሉት። ሕዝብን ከጸጥታ ችግር በማውጣት ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚደረገው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
የታጣቂ ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸውን አካባቢዎች በመዝጋት ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አዛዡ በተሠራው የማጨናነቅ እና የማጣበብ ሥራ በርካታ ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጥተዋል ብለዋል። የመተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት የሰላም አማራጮችን የሚጠቀሙት የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ፣ የሰላም አማራጭን በማይጠቀሙት ላይ ደግሞ የሕግ ማስከበር እርምጃ ለመውሰድ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰሜን ጎጃምን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ከጸጥታ ግብረ ኃይሉ ጋር በተሠራው ሥራ የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉን ገልጸዋል።
በከተማዋ ሰላም አሉታዊ ተጽዕኖ በሚያደርሱ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል። በከተማዋ የሚካሄዱ የትኛውም ኹነቶች በሰላማዊ መንገዶች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል።
አኹን ላይ በከተማዋ የተፈጠረውን ሰላም የሚያደናቅፍ ችግር እንዳይፈጠር እንደሚሠራም አመላክተዋል። የጸጥታ ኃይሉ በቅንጅት የከተማዋን ሰላም እያስከበረ ነው ያሉት አዛዡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባኤ በባሕር ዳር የሚያካሂደው የሰላም ኮንፈረንስ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
ለከተማዋ ሰላም የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በብሎክ አደረጃጀት ሰላሙን እየጠበቀ መኾኑን ተናግረዋል። ከማኅበረሰቡ ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። በከተማዋ ዙሪያ ከሚገኙ ዞኖች ጋር እና ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአድማ መከላከል ፖሊስ የሰው ኀይል አሥተዳደር ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር መልካሙ የሽዋስ እንደ ክልል ሰላምን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። የጸጥታ ኀይሉ በሠራው የተቀናጀ ሥራ አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል ነው ያሉት። አኹንም ቀሪ ሥራዎች አሉ ያሉት ኀላፊው ነገር ግን በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ ሕዝቡ ወደ መደበኛ ሥራው እየተመለሰ ነው ብለዋል።
የክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለአንድነት፣ ለሰላም እና ለአብሮነት የሚሠራው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚያካሂደው የሰላም ኮንፈረንስ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። የ101ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ሌትናል ኮሎኔል አየልኝ አስናቀ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል።
የመጣው ሰላም ዝም ብሎ የመጣ አለመኾኑንም ገልጸዋል። በቅንጅት በተሠራው ሥራ በክልሉ የተሻለ ሰላም በመፈጠሩ ደስተኛ ነኝ ብለዋል። ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። መስዋዕትነት የተከፈለበት ሰላም ዘላቂ እንዲኾን በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል። በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት በሁሉም መስክ ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በአንድነት መሥራት የትኛውም ሥራ በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ያስችላል ነው ያሉት።
በሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግሮ የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል እውነታውን በመገንዘብ ለሰላም መረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል። አኹን ላይ ለጸጥታ ኀይሉ መረጃ በመስጠት፣ በመደገፍ እና አብሮ በመሥራት ውጤታማ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ባንዳዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሠሩ ነው ያሉት ሌትናል ኮሎኔሉ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት የሚፈጽም ኃይል ሁሉ አስፈላጊውን መልስ ያገኛል ብለዋል። የጸጥታ ኃይሉ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ በመገንዘብ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መኾኑን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን