የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ትግበራው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራትን ይጨምራል።

70

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከመንግሥት መዋቅር የሥራ ኀላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ጋር በመንግሥት አገልግሎት እና ስታንዳርድ ሪፎርም አተገባበር ላይ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። የተሠሩ ተግባራት ቢኖሩም አሁንም ግን በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ነው የገለጹት።

መንግሥት ለሲቪል ሰርቪሱ መሻሻል የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ እየተገበረ ነው ብለዋል። ይህ መድረክም የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደርን ሪፎርም በአማራ ክልል የመተግበሪያ አንዱ አካል እንደኾነ ነው የተናገሩት።

መንግሥት እና ሠራተኛውን እንዲሁም ሠራተኛውን እና ተገልጋዩን በማገናኘት ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እና የመልካም አሥተዳደርን ችግር ለመቅረፍ ንቅናቄው ጥቅም እንዳለውም ገልጸዋል። ይህንን ውጤታማ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።

በተመረጡ ስምንት ሴክተሮች የተጀመረው ይኼው ማሻሻያ በሂደትም ተሞክሮ እየተቀመረ በሁሉም ተቋማት እንደሚተገበር ገልጸዋል። በዚህም አገልግሎት አሰጣጡን በዲጂታላይዜሽን በማሳለጥ የሕዝብ ተገልጋይነት እንደሚያድግ ይጠበቃል ብለዋል።

ይህ ተግባር ስኬታማ እንዲኾን በተለይ መሪዎች በአርኣያነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው አቶ ሲሳይ የገለጹት። የሪፎርሙ አካል በኾነው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን የማጣራት ሥራም የሥራ ኀላፊዎች እና ቡድን መሪዎች በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ለሌላው ማሳየት አለባቸው ነው ያሉት።

ሀገርን፣ ሕዝብን እና ራሱን ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዘውን ሰው ጭምር የሚጎዳ መኾኑን በመገንዘብ ሁላችንም አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይፈለጋል ብለዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር ሽፋኑ ፖለቲካዊ ይሁን እንጂ አብዛኛው ችግር የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግር መኾኑን አቶ ሲሳይ አንስተዋል።

በምንሰጠው አገልግሎት የምንፈታው ችግር ቁጥር መጨመር አለበትም ብለዋል። አሁን ያለው አገልግሎት ያለበትን ሁኔታ አገልግሎት አላገኘሁም ከሚለው ሕዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት አኳያ ቃኝቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ማሻሻያውን በመላው ሠራተኞች ንቅናቄ በውጤታማነት በመሥራት፣ መንግሥት እና ሕዝብን በማገናኘት እና ልማትን እውን በማድረግ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እና መልካም አሥተዳደርን ማስፈን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ መንግሥት ሕዝብን ለማገልገል ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ማውጣቱን ተናግረዋል። ለተግባራዊነቱም የመንግሥት ሠራተኞች ልማት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

በየጊዜው የሰው ኃይል ልማቱ እያደገ ቢኾንም በሚፈለገው ልክ ግን አለመኾኑን ገልጸዋል። የመንግሥት ሠራተኛው የተሰጠውን ሥራ ፈጽሞ የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ፍላጎት በማርካት እና ሕዝብ እና መንግሥትን በማገናኘት በኩል ውስንነት እንደሚታይ ጠቅሰዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፖሊሲ ጸድቆ በትግበራ ላይ መኾኑን የገለጹት አቶ አስሜ በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው የለውጥ ትግበራ ወደ ከተሞችም መድረሱን ገልጸዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር በሚያድገው ልክ የአገልግሎት አሰጣጡ ጥራት እና ስፋት አለማደጉን ገልጸዋል። አንዳንድ አገልግሎቶች ወደ ኋላ እየቀሩ መኾኑንም አንስተዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ከሚፈለገው የፖሊሲ አተገባበር አኳያ እየተቃኘ መዘጋጀቱንም አቶ አስሜ ተናግረዋል። ባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር ያለበት ከተማ መኾኑን እና የሚፈለገውን የመንግሥት አገልግሎት ለተጠቃሚው ሕዝብ እየሰጠ ነው ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል። የሕዝብ አገልግሎት እየጨመረ ወይስ ቅሬታ እየጨመረ ነው የሚለውንም አይቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በመድረኩ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለን ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የሪፎርም ሥራ ተጀምሯል።
Next articleዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሠራ ነው።