የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የሪፎርም ሥራ ተጀምሯል።

16

ከሚሴ: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ በመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በከሚሴ ከተማ ምክክር አካሂዷል።

በመድረኩ የክልል እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደሮች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የጨፋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋጡማ ሀሰን በወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች የሪፎርሙ መጀመር በመንግሥት ተቋማት ተገቢው ሙያተኛ በተገቢው ቦታ ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የደዋጨፋ ወረዳ ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኡመር አወል ሕዝቡ የሚያቀርበውን የመልካም አሥተዳደር ችግር ለመቅረፍ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ስለሚገባ ሪፎርሙ ይህን ለማሳካት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አደም የሱፍ የመንግሥት ሠራተኛው ሪፎርም ሥራ ያስፈለገው በየጊዜው ሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እያገኘ አለመኾኑ በመረጋገጡ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በማለም ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲውን በማሻሻል ዘርፉን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ኀላፊው ተናግረዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበኩላቸው የተቀናጀ እና የተደራጀ የሰው ሀብት ልማት ሥርዓትን በመፍጠር የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሳለጥ ሪፎርሙ በተገቢው ኹኔታ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በማጥራት በተገቢው ቦታ ተገቢውን ሰው ለማስቀመጥ የተጀመረው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን የማጥራት ሥራ እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች በትኩረት እንደሚሠራም ዋና አሥተዳዳሪው አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሴቶች በችግሮች አልፈው ሃብት ማፍራት መቻላቸው በቀውስ ውስጥ ለሚያልፉ ሴት መሪዎች አስተማሪ ነው” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ
Next articleየሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ትግበራው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራትን ይጨምራል።