
ደሴ: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ ሴት መሪዎች ከደረሰባቸው ጫና እና ድብርት እንዲላቀቁ የሚያስችል የቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ መሪነት ሥልጠና ለሦስት ተከታታይ ቀናት በደሴ ከተማ ተሠጥቷል።
በሥልጠናው የመጨረሻ ቀንም ሠልጣኞቹ በከተማዋ በሴቶች የተሠሩ ተግባራትን እና በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝተዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው በከተማዋ በከብት እርባታ፣ በባልትና ሙያ የተሠማሩ እና ያገለገለን ፕላስቲክ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በትንሽ ገንዘብ ተነስተው ሃብት ማፍራት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በተሠማሩበት መስክ ተጠቃሚ መኾናቸውን የገለጹት ሴቶቹ በቀጣይም ሥራቸውን አስፋፍተው በመሥራት ለሌሎች ወገኖችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሠሩ ነው ያብራሩት። በጉብኝቱ የተገኙ ሴት መሪዎችም የተሠሩ ተግባራት ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ የሚኾኑ ናቸው ብለዋል። በከተማ አሥተዳደሩ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እና ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ እንደኾነ ተመልክተናል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ”ሴቶች በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፈው ሃብት ማፍራት መቻላቸው በቀውስ ውስጥ ለሚያልፉ ሴት መሪዎች አስተማሪ ነው ብለዋል።
የተሠራው ተግባር ሴቶች እና ታዳጊዎች የሚያደርጉትን ሕገ ወጥ የውጭ ሀገር ጉዞ በማስቀረት በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ሊኾን የሚችል እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አንተነህ ጸጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን