
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ የፌዴራል ፖሊስ መኮንኖች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ የሁኔታ መነሻ በማቅረብ ከሁሉም የጸጥታ ተቋማት እና የደኅንነት የጸጥታ ግብረ ኃይል ጋር መገምገማቸውን ተናግረዋል። በክልሉ የጸጥታው ሁኔታም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ውጤት እያስመዘገበ መኾኑን አመላክተዋል። “ሁሉም በየተሰማራበት ያስመዘገበው ውጤት አሁን ለተመዘገበው አንጻራዊ ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል” ነው ያሉት።
ቀበሌዎችን እና የተወሰኑ መተላለፊያ ቦታዎችን የማጽዳት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በርካታ የጽንፈኛው ኃይል አባላት እየፈረሱ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀሙ እየገቡ መኾናቸውን ገልጸዋል። መንግሥትም በቂ ዝግጅት አድርጎ እየተቀበለ መኾኑን ተናግረዋል።
በጠረፍ አካባቢ ከሩቅ እና ከቅርብ ጠላቶች ጋር የሚሠሩ ኃይሎች አሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ከታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ የሚቀበሉ መኖራቸውንም ገልጸዋል። በየትኛውም መመዘኛ አንድነት መፍጠር የማይችሉ አካላት አንድነት ፈጠርን በማለት የባንዳነት ሥራ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
ለቀድሞ ጠላቶቻችን በፈቃደኝነት ተቀጥረው ለመሥራት ጥረት ቢያደርጉም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል መንቀሳቀሻ አጥተዋል ነው ያሉት። ሕዝቡ ከጎናችን ተሰልፏል ያሉት ኮሚሽነሩ አብዛኛው ሕዝብ ሰላም ወዳድ በመኾኑ እና ሰላም አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመኾኑ ከመንግሥት ጋር በጋራ እየሠራ ነው ብለዋል። ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሥራቱ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ በውስጥም በውጭም እየተቀየረ መምጣቱንም ገልጸዋል። በአማራ ክልል የሚካሄደው የሃይማኖት ጉባኤ የሰላም ኮንፈረንስ እና የተጀመረው የተማሪዎች ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቂ ዝግጅት በማድረግ በሁነቶች ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የጸጥታ እና የጋራ ግብረ ኃይል በጋራ በመወያየት የጋራ አቅጣጫ መስጠቱንም ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም በአግባቡ የለየ፣ የሚቀሩ፣ እንዳንድ ቋጠሮዎችን ለመፍታት እና ብቅ ጥልቅ የሚልን ኃይል በተገቢው መንገድ ለመቆጣጠር መግባባት ላይ የደረስንበት ውይይት ነው ብለዋል። የሰላም አማራጩን እየተጠቀመ የሚመጣውን ኃይል ደግሞ በአግባቡ በመያዝ፣ በማስተማር እና መልሶ የማቋቋም ሥራው የተቀላጠፈ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።
የጸጥታ ኃይሉም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ዝግጅት እየሠራ መኾኑንም አመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን