የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ በአገልጋይነቱ የላቀ የመንግሥት ሠራተኛ ለመፍጠር አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ።

27

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ወደ ተግባር ለማስገባት ያለመ ውይይት በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ አገልጋይ የኾነ የመንግሥት ሠራተኛ ለመፍጠር የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል። በጸጥታ ችግር ዉስጥ ኾነን የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ለመተግበር ስንጥር ቆይተናልም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ሰላምን የማፅናት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት አቶ መካሻ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም ትግበራ ደግሞ የበለጠ አገልጋይ የመንግሥት ሠራተኛን መፍጠር ያስችለናል ነው ያሉት፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ዋና አላማ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ ቀዳሚ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በዕውቀት እና በክህሎት የተሻለ እንዲኾኑ ማድረግ ሌላኛው ሲኾን ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል አገልግሎት አሠራርን ማስፋትም የሪፎርሙ ዋና አላማ ስለመኾኑ ተመላክቷል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሜሮን አበበ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተናባቢ የኾነ አደረጃጀት ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተናባቢ አደረጃጀቶች አለመኖራቸው ለሪፎርሙ መነሻ ነው ብለዋል። ይህንን ለማስተካከል ሪፎርሙ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎት ለመስጠት በአንድ ማዕከል የሚናበቡ ተቋማት አለመደራጀታቸው ተገልጋዮችን ለእንግልት እና ለእጅ መንሻ አጋልጧቸዋል ነው ያሉት። እነዚህ ችግሮች በሪፎርሙ ይቀረፋሉም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ወንዲፍራ ዘዉዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምሰሶ ነው።
Next articleጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች