
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ከተማ ተዘዋውረው የፈተናውን ሂደት ተመልክተዋል። ለተማሪዎች እና መምህራን እንኳን ለ2017 ዓ.ም ክልላዊ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በሰላም አደረሳችሁም ብለዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ ፈተናው በክልሉ በሁሉም ዞኖች እየተሰጠ ነው ብለዋል። በትምህርት ቤት ደረጃ 2 ሺህ 275 ትምህርት ቤቶች እያስፈተኑ ይገኛሉ ነው ያሉት። አሁን ላይ 130 ሺህ 280 ተማሪዎች ፈተናውን በመውሰድ ላይ ናቸው ብለዋል። ፈተናው በሰላም እንደመጀመሩ በሰላም እንዲጠናቀቅም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ዶክተር ሙሉነሽ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) እንዳሉት እንደባሕር ዳር ከተማ በ49 ትምህርት ቤቶች ፈተናው እየተሰጠ ይገኛል። 7 ሺህ 288 ተማሪዎች ደግሞ በመፈተን ላይ ናቸው። ከዚህም ውስጥ 4 ሺህ 74 ተማሪዎች ሴቶች ናቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ መሪዎች የፈተናውን ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን