
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ትምህርት ዋነኛ የድህነት መውጫ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል። በሀገራችን የትምህርት ሥርዓት በግሉ ዘርፍ ጭምር እንዲሰጥ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል። ተቋም ገንብቶ፣ የትምህርት መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ በትምህርት ዘርፍ ለመሠማራት ለሚፈልግ የግል ባለሀብት የትምህርት ፖሊሲው ያበረታታል።
ምንም እንኳን በቂ ነው ባይባልም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግል ትምህርት ቤቶች በቁጥር እየተበራከቱ፣ የመንግሥትን ጫና እያቃለሉ፣ እንዲሁም የኅብረተሰቡን አማራጭ እያሠፉ መጥተዋል። ይሁን እንጂ የግል ትምህርት ቤቶች በየወቅቱ ማኅበረሰቡን በሚገባ ሳያወያዩ የትምህርት ክፍያ ይጨምራሉ በሚል በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታን ሲፈጥር ይስተዋላል።
ይህንን መሰረት በማድረግ ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ክፍያ ማሻሻያ ለማድረግ ውይይቶችን እያደረጉ ነው። በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የብጹዕ አቡነ በርናባስ ቤዛ ብዙኃን ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ማረው ደርሶ በቀጣይ በጀት ዓመት ለሚደረገው የትምህርት አሰጣጥ ክፍያ ለመጨመር ወላጆችን ጠርተው ውይይት መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ከአሁን በፊት ሲያስከፍል የነበረው ክፍያ ዝቅተኛ መኾኑን አንስተዋል። ይህም በ2018 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር የማያስችል ስለመኾኑ ተናግረዋል። ይህንን መሠረት አድርጎ በቀጣይ ትምህርት ቤቱን ሊያሠራ የሚችል የክፍያ ጭማሪ ተመን ለወላጆች ይዞ መቅረቡን ርእሰ መምህሩ አንስተዋል። የቀረበው የክፍያ ጭማሪ ሀሳብ በቀጣይ የሚኖረውን የመማር ማስተማር ሂደት ያሳልጣል በሚል እንደኾነ አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቱ ያቀረበው የክፍያ ጭማሪ ሀሳብ በ2018 የትምህርት ዘመን ለመሥራት ያቀደውን ተግባር ለማሳካት እንደኾነም ነው የገለጹት። ጭማሪውም ወላጆች መጋራት የሚገባቸውን ወጭዎች ብቻ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል። በውይይቱ ወቅት የቀረበውን የክፍያ መነሻ ወላጆች መቀበል ባለመቻላቸው ውሳኔ እንዲሰጥበት ለትምህርት መምሪያው ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮ-ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ቁጥር ሁለት ርእሰ መምህር ገበያው መላክ ትምህርት ቤታቸው ባለፈው ዓመት ክፍያ አለመጨመሩን ገልጸዋል። ለ2018 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ለወላጆች አቅርቦ ማወያየቱን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ ያቀረበው ጭማሪ በቀጣይ የትምህርት ዘመን የተሻለ ሥራ ሊያሠራ የሚችል ጭማሪን ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ወላጆች ከተወያዩ በኋላም የራሳቸውን አቅርበዋል፤ በተመሳሳይ ለወላጅም ለትምህርት ቤቱም ተወካይ የኾኑት የወላጅ መምህር ኅብረት ደግሞ የራሳቸውን ውሳኔ ማቅረባቸውን አንስተዋል። ሦስቱም የክፍያ ሀሳቦች ለከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ተልከው ውሳኔ እየጠበቁ መኾኑንም አቶ ገበያው አብራርተዋል። ይህም ትምህርት መምሪያው ባስቀመጠው አሠራርና መመሪያ መሠረት የተከናወነ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
የክፍያ ሁኔታዎችም ኾነ ሌሎች የመማር ማስተማር ሂደቶች ከወላጅ መምህር ኅብረት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን መሰረት ያደረጉ እንደኾነም ጠቁመዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ትበይን ባንቲሁን የግል የትምህርት ተቋማት ክፍያን ለመወሰን ከወላጆች ጋር ውይይት የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ውይይቶችን የሚያደርጉበት ወቅትም እስከ ግንቦት 30 ድረስ ብቻ እንዲኾን የጊዜ ገደብ የተሰጠ መኾኑንም ጠቁመዋል። በዚህ መሠረትም በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶች ወላጆችን የሚያወያዩበት ወቅት ተጠናቅቋል ማለት ነው። ከሰኔ 1 ጀምሮ ደግሞ የትምህርት መምሪያው ባለሙያዎች መረጃዎችን እያጣሩ በትክክለኛው መንገድ ሕዝብን አወያይተው ጭማሪ ያስወሰኑት ይለያሉ። በመቀጠልም በመምሪያው ማኔጅመንት የሚፀድቅ ይኾናል ነው ያሉት።
የመጡትን ቅሬታዎች እና ተጨባጭ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ ባለሙያ ወደ ተቋማት በመላክ የሚረጋገጥበት አሠራር መኖሩንም ተናግረዋል። ማንኛውም ትምህርት ቤት ክፍያ የሚጨምረው ወላጆችን አወያይቶ ሲስማሙበት ብቻ መኾኑን ነው የገለጹት። ይህም ያወያየበት ሰነድ ተረጋግጦ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ከአጸደቀለት ብቻ መኾኑን አንስተዋል። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ጭማሪ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል።
አላስፈላጊ ጭማሪ በሚደረግበት ወቅት ወላጆች ከሰኔ 1 ጀምሮ በወላጅ ኮሚቴ አደረጃጀቶች አማካኝነት ቅሬታቸውን ለትምህርት መምሪያው ማቅረብ እንደሚችሉ አመላክተዋል።
ማኅበረሰቡም የሚያነሳቸውን የመማር ማስተማር ጥያቄዎች አደረጃጀቶችን እና ኮሚቴዎችን በመጠቀም በአግባቡ ለመምሪያው ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበዉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን