
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰኔ 04/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ ሊካሄድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ አንድነት እና የተባበረ ክንድ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን አስከብራ መኖሯን ገልጸዋል፡፡
ይህ አንድነትም ታላቅ እንድትኾን እና ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ማድረጉንም ነው የተናገሩት፡፡ የአድዋ ድልንም በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ላይ የሕዝቦቿ አንድነት ችግር ያጋጠመው በመኾኑ ግጭቶችን ለማስቆም የሃይማኖት ተቋማት ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል። ሕዝቡን በማሰባሰብ እና የመንግሥትን መሪዎች ጭምር በመያዝ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ወደ አላስፈላጊ መስመር እየሄደ ስለኾነ የሃይማኖ አባቶች መክረው መመለስ አለባቸው ያሉት መልአከ ብርሃን ፍስሐ፣ ሕዝቡ የሚጠይቀውን ጥያቄም በመመካከር፣ በመወያየት እና በመደራደር መፈጸም አለበት ነው ያሉት፡፡ እርስ በርስ በመገዳደል እና የሀገር እና የሕዝብን ሃብት በማውደም የሚፈታ ችግር የለም ብለዋል።
በሀገር ደረጃ ከተደረገው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ቀጥሎ የሚካሄድ ጉባዔ መኾኑን ያነሱት ሰብሳቢው ተሞክሮዎችን በመቀመር ወደ ክልላችን ነባራዊ ኹኔታ በመመለስም ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡ በጉባዔው የዓለም የግጭት አፈታት ተሞክሮ እና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ ታላላቅ ሰዎች እና የመንግሥት አካላት መልዕክት እንደሚስተላልፉም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጀውሀር ሙሐመድ ኢሣ የሰላም ጉባዔው ከፌዴራል ጀምሮ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልልም የሰላም ጉባዔውን ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት፡፡
የሃይማኖት አባቶች የሕዝብ አባት መኾናቸውን ተናግረዋል። በአንድ ላይ ኾነው ለሰላም ዘብ መቆማቸውን ለሕዝቡ ማሳየት አለባቸው ብለዋ። ከሃይማኖት አባት የሚወጣ ስለሌለ የሃይማኖት አባቶች የሕዝብን ችግርና መከራ ለመታደግ በአንድ ላይ ቆመው መታየት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
ልጆቻችን ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ ማድረግም ይጠበቅብናል ያሉት ሼህ ጀውሀር አማኞች ወደ ሃይማኖቸው ተመልሰው ሰላማዊ ሰው እንዲኾ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡ በሰሜን ምዕራብ ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከዚህ በፊትም በሰላም ጉዳዮች ላይ ሢሠራ እንደነበር ገልጸዋል።
አኹን ላይም በክልሉ የተከሰተውን የሰላም እጦት ምክንያት በማድረግ ሰላም ወዳድ ኃይሎችን የሚያሳትፍ ጉባዔ ሊካሄድ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከፌዴራል፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከየዞኑ የሃይማኖት አባቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ሁሉም ሰዎች ለጉባዔው መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጠይቀዋል፡፡
የሃይማኖቶች ዋና ዓላማ ለተከታዮቻቸው ሰላምን ማስተማር ነው ያሉት መጋቢ ገብሬ ግጭቶችን በመመካከር እና በመወያየት ችግሮችን መፍታት ነው ብለዋል፡፡ የሰላም እጦቱ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ የፈጠረው ችግር መውጫው መንገድ ሰላም መኾኑን በመገንዘብ የሃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም መናገር እና ሰፋ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ አለባቸው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ: ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን