ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት እየኾነ ነው።

20

ጎንደር: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።

በንቅናቄ መድረኩ የከተማ አሥተዳደሩ እና የክፍለ ከተማ የሥራ ኀላፊዎችና የቡድን መሪዎች ተገኝተዋል። በአማራ ክልል ከ500 ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች እና ከ7 ሺህ በላይ ተቋማት እንዳሉ በውይይቱ ተገልጿል።

ዘመኑ ከሚፈልገው ፈጣን ለውጥ ጋር የተጣጣመ የሰው ኃይል፣ የመንግሥት አገልግሎት እና የአሥተዳደር ሪፎርምን መገንባት እንደሚያስፈልግም በዕለቱ ተነስቷል።ተግባሩን በቅርቡ ለመጀመር የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ ተናግረዋል።

የሪፎርሙ አስፈላጊነት ከፌደራል እስከ ቀበሌ የተናበበ አሠራር መዘርጋትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ከተቋም ተቋም ኀላፊነትን የመለየት፣ የሕዝብ ብዛትን እና የቆዳ ስፋትን መሠረት ያደረገ አደረጃጀትን መፍጠር፣ የሥራ ምዘና አፈጻጸም ሥርዓትን ማዘመን፣ የሥራ መደብ እና ተፈላጊ ችሎታን ወጥ ለማድረግ እንደሚያግዝም ተገልጿል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ተገልጋዩ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን አቶ ነጻነት ተናግረዋል። ወቅቱ ከሚጠይቀው የአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የሪፎርሙ መተግበር ወሳኝ በመኾኑ ተግባራቱን ለመፈጸም ዝግጁ መኾናቸውን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ጽዳት ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኾነዓለም አሻግሬ ገልጸዋል።

የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት ይገባል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰዒድ የሻው ናቸው። ተግባሩን በሚፈለገው ልክ ለመከወን የተቋማትን ትብብር ይጠይቃል ነው ያሉት።

የማኅበረሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሳካት ሲቪል ሰርቫንቱ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መኾኑን ያስታወሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ናቸው። የከተማ አሥተዳደሩ ለሪፎርሙ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ተግባራዊ የሚደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት እንደሚያስችሉም ገልጸዋል። የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዲሞክራሲ እና ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ( ዶ.ር) ናቸው። ሲቪል ሰርቪስ የጀመረውን የለውጥ ተግባር ዳር የማድረስ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ዘጋቢ: ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየወልድያ ከተማ አሥተዳደር ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ማጣራት ጀመረ።
Next articleየሃይማኖት ተቋማት ስለ ሰላም የሚመክሩበት ጉባዔ ሊካሄድ ነው፡፡