
ደብረማርቆስ: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በ2015 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው የመሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት እስካሁን ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ ባለሃብቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እያከናወኑ ነው።
በቤት እና በቢሮ እቃዎች ማምረት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ ላቀ በላይ ለኢንቨስትመንት ሥራው አስፈላጊ የኾኑ የመሠረተ ልማቶችን ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው ለመገንባት ሥራዎችን እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። አቶ ላቀ የግንባታ ግብዓቶችን በማቅረብ ለመንገድ ሥራው ቅድሚያ ሰጥተው እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ እንደገና አማረ በከተማው ቀደም ብሎ ከ168 በላይ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይ በተለያየ ምክንያት በማምረት ላይ የሚገኙ 32ቱ ብቻ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ባለሃብቶቹ ያለባቸውን የመሠረተ ልማት ችግር በመቅረፍ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም አብራርተዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኅላፊ ተመስገን ተድላ ባለሃብቶች የሚያነሷቸውን የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመፍታት ከባለሃብቶች ጋር በቅንጂት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሽ ተመስገን ለኢንዱስትሪ መንደሩ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የመብራት ዝርጋታ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ለኢንቨስትመንት ሥራው አስፈላጊ የኾኑ ተጨማሪ የመሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከ900 ሄክታር በላይ መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ በመኾኑ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲያለሙም ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን