
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ እንዳለው ታምኖበት በጉጉት እየተጠበቀ ያለ ነው። በሀገሪቱ ላይ ያደሩ፣ የቆዩ እና የነበሩ ቁርሾዎችን መፍትሔ ለመስጠትም ሚና እንደሚኖረው ተስፍ ተጥሎበታል። ይህ ዕውን የሚኾነው ግን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ጠጠር መወርወር ሲችል ነው።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እውነትም ለሀገር መፍትሔ ይኾን ዘንድ ታድያ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና የሚናቅ አይደለም። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ ሊቀመንበር እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀገር ትምከር በሚል አስተሳሰብ አጀንዳ እያሠባሠበ ይገኛል ብለዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርን ሊያሻግሩ የሚችሉ ሀሳቦችን፤ ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ ቁም ነገሮችን እና ያሉንን ተቃርኖዎች ልንፈታባቸው የሚችሉ አጀንዳዎችን ማስመዝገብ አለብን ነው ያሉት። በዚህ ሂደት ውስጥ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳቸውን እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል። በቀጣይም በመቻቻል መንፈስ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኔ ሃሳብ ብቻ ይደመጥ ከሚል አስተሳሰብ ወጥተን መሥራት ይኖርብናል ነው ያሉት አቶ ተስፋሁን። በምክክር ውስጥ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ አይኾንም ብለዋል። ሁላችንም አሸናፊ የሚያደርገንን መንገድ፤ ሀገር አሸናፊ የምትኾንበትን ስልት መደገፍ አስፈላጊ እንደኾነ ነው የገለጹት አቶ ተስፍሁን። “ሀገር አሸናፊ የምትኾንበት ዘዴ ደግሞ መመካከር ነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ተቃርኖዎች በአጀንዳ እየተያዙ ነው ብለዋል አቶ ተስፋሁን። ጫካ የገቡ ወንድሞቻችን የሚያነሱት አጀንዳ ሳይቀር በምክክር ኮሚሽኑ እየተነሳ እንደኾነ ነው የገለጹት። በየትኛውም መንገድ ሀሳቦች ወደ ምክክር መምጣታቸው መልካም ነው ብለዋል። ምንም አይነት ሰበብ ሳይበዛ ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን አጀንዳቸውን ለምክክር ኮሚሽኑ ማስመዝገብ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በዚህ ተግባር ላይ የፓርቲዎች ሚና የተገኘውን ዕድል ለመጠቀም ማገዝ ይኖርብናል ነው ያሉት። ይህን በማድረግ ሂደት የሚከፈል ዋጋ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ሀገርን ማሻገር ከተቻለ ታሪካዊ ዋጋ ይኾናል ነው ያሉት። የኔ ሀሳብ ብቻ ይደመጥ የሚል አስተሳሰብ ሀገርን ያወድማል ብለዋል። ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከተፈለገ የትኛውም ሀሳብ ይኑረን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ማገዝ ይኖርብናል ነው ያሉት። ዕድሉን መጠቀም ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።
ሌላው ለአሚኮ ዲጅታል ሚድያ ሀሳባቸውን የሰጡት የአብን ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ጸጋዬ ናቸው። አብን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተዋናይ ኾኖ ይደግፋል ብለዋል። ከ47 ገጽ በላይ የያዘ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በሚል አጀንዳችንን ይዘን በወቅቱ አቅርበናል ነው ያሉት። ችግሮቻችን የሚፈቱት በውይይት እና በንግግር ስለኾነ ምክክር ኮሚሽኑን መደገፍ በእጅጉ ተገቢ ነው ብለዋል።
ይህ ዕድል ሊያመልጠን የማይገባ እና እንደ ሕዝብ ልንደግፈው የሚገባ እንደኾነ ነው የተናገሩት አቶ መልካሙ። መላው የአማራ ሕዝብ ተመሳሳይ ሊባሉ የሚችሉ ጥያቄዎች ያሉት ቢኾንም የሚመለሱበትን መንገድ ያሰብንበት ኹኔታ የተለያየ ኾኗል የሚሉት ምክትል ሊቀመንበሩ ማሰሪያ ሊኾን የሚችለው ግን ምክክር ነው ብለዋል።
በቀጣይም በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ሀሳብ ቢጠቀሙበት መልካም ይኾናል ነው ያሉት። ወንድሞቻችን ለኮሚሽኑ ጥሪ አወንታዊ ምላሽ መስጠት አለባቸው ብለን አናምናለን ነው ያሉት።
የምክክር ኮሚሽኑ እውነትም የሀገር መፍትሔ ይኾን ዘንድ ነጻ፣ ገለልተኛ እና አሳታፊ አካሄድን መከተል አለበትም ብለዋል አቶ መልካሙ።
ይህ በተግባር ላይ ከዋለ ጥያቄዎች በእርግጠኝነት መልስ ያገኛሉ ነው ያሉት። ኮሚሽኑ እስካኹን የመጣበትን መንገድ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን