
እንጅባራ፡ ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን – አሚኮ በአዊኛ ቋንቋ የራዲዮ ሥርጭት የጀመረበትን 20ኛ ዓመትን አስመልክቶ በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው።
በፕሮግራሙ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ አሚኮ በ1987 ዓ.ም በውስን የሰው ኃይል እና በወቅቱ የቴክኖሎጂ አቅም በበኩር ጋዜጣ ሥራ የጀመረ ተቋም ነው ብለዋል።
“ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን” በሚል መሪ ሃሳብ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አሥተዳደር እንቅስቃሴዎችን ለሕዝብ እያደረሰ ያለ ተቋም እንደኾነ ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅትም 1 ሺህ የሚጠጉ ጋዜጠኞችን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችን አቅፎ እየተጋ ያለ ነው ብለዋል። የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች ወደ አድማጭ ተመልካቾች እና አንባቢዎች እያደረሰ ይገኛል ነው ያሉት።
አሚኮ በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከታጠቁ ተቋማት ቀዳሚ ሚዲያ ነው ብለዋል። በሰባት የራዲዮ ጣቢያዎች፣ በአራት ጋዜጦች እና በሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ እያደረሰ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በቅርቡም አሚኮ የልጆች የቴሌቪዥን ቻናልን ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይ የኅብረተሰቡን ለውጥ ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በ30 ዓመታት ጉዞው የአዊ ብሔረሰብን ጨምሮ በክልሉ አካባቢዎች ከፍ ያሉ ተግባራትን እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው አዊኛ የራዲዮ ሥርጭት የአዊን ቋንቋ፣ ወግ እና ባሕል እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የሥርጭት ሰዓቱን እያሳደገ ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ አዊኛ ራዲዮ የአዊ ወግ፣ ባሕል፣ ቋንቋ እና ሃብቶችን ለዓለም እንዲተዋወቁ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ኀላፊነት እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ የቋንቋ ብዝኀነቶችን ሃብት አድርጎ መጠበቅ ይገባልም ብለዋል። ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በእንጅባራ ከተማ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እንዲገነባ 1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቷል ብለዋል።
የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም አዊኛ ራዲዮ ለቋንቋው እድገት የተወጣው ኀላፊነት ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን