
ደሴ: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በክልሉ ባለው ወቅታዊ ችግር ሴት አመራሮች ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጫና እንዲላቀቁ የሚያስችል የቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ሥልጠና በደሴ ከተማ እየሰጠ ነው። በሥልጠናው ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ሴት መሪዎች እየተሳተፉ ነው።
በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ ሴቶችን በተለያዩ መሰኮች ማብቃት እና የመሪነት ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ ለሀገር ግንባታ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ በርካታ ጠንካራ ሴት መሪዎች መኖራቸውን ያነሱት ከንቲባው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በክልሉ የተከሰተው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በማኅበረሰቡ ላይ በርካታ ችግሮችን ማድረሱን ገልጸዋል።
ከደረሱ ችግሮች በተጨማሪ በሁሉም የኅበረተሰብ ክፍሎች ላይ የሥነ ልቦና ጫና ማሳደሩን አውስተው በሴቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ተደራራቢ መኾኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ሴቶች በደረሰባቸው ድብርት፣ ፍርሀት እና ጭንቀት የተነሳ ወደ አመራርነት ለመምጣት የፍላጎት ማጣት ተስውሏል ነው ያሉት።
በወቅታዊ ችግሩ ምክንያት የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል የሴት አመራሮች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ ሥልጠናው መሠጠቱ ተግባራቸውን በንቃት እና በአዲስ መንፈስ እንዲሠሩ እና በተሰማሩበት መስክ ሥራቸውን በውጤታማነት ለመፈፀም እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል።
በሥልጠናው ከ280 በላይ ሴት አመራሮች እየተሳተፉ ነው። ሰልጣኞቹ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እና እያጠጋመ ያለውን ችግር እንደመስፈንጠሪያ በመውሰድ የመፍትሄው አካል እንዲኾኑ ለማስቻል ፋይዳው ከፍተኛ እንደኾነ ቢሮ ኀላፊዋ አብራርተዋል።
ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱም ለችግር ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል። ሥልጠናው ለሦሥት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ይኾናል።
ዘጋቢ ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!