ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወረታ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የልማት ሥራዎችን መርቀው ሥራ አስጀመሩ።

31

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወረታ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የልማት ሥራዎችን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክርቤት ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ መርቀው ሥራ ያስጀመሯቸው የወረታ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና በወረታ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባውን የማስፋፋፊያ ፕሮጄክት ነው።

የወረታ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ ከጀመረ ቆይቷል። በወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይመረቅ መቆየቱ ተነግሯል። ዛሬ በከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተደርጎለታል።

ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የሆስፒታሉን የሥራ እንቅስቃሴም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የወረታ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ባለ ሦስት ወለል (G+3) ሕንጻ ነው። 20 የመማሪያ ክፍሎች አሉት።

በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል አስተባባሪነት የተሠራው ትምህርት ቤቱ 17 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ከአኹን በፊትም በትምህርት ቤቱ አስተባብረው የማስፋፊያ ሕንጻ ማስገንባታቸው ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ የራሱን ሰላም እንዲጠብቅ የሚያስችል ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleበወቅታዊ ችግሩ ምክንያት የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል የሴት አመራሮች ሚና ከፍተኛ ነው።