
ወልድያ: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያበለፀገውን የሁነቶች ኦንላይን ምዝገባ መተግበሪያ በወልድያ ከተማ አስጀምሯል።
የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ ተቋሙን በማዘመን ጥራት ያለው መረጃ ለማመንጨት የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው አገልግሎት የወረቀት፣ የጊዜ እና የጉልበት ብክነት እንዲሁም የመረጃ ጥራት ችግር ነበረበት ያሉት ኀላፊዋ በዚህ ዓመት በ4 ከተማ አሥተዳደሮች በተጀመረው የኦንላይን ምዝገባ በ122 የምዝገባ ጣቢያዎች ከ40 ሺህ በላይ ኩነቶች ምዝገባ ተከናውኗል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብቻ የኦላይን ምዝገባ ከጀመሩ አራት ከተሞች ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ መቆጠብ ተችሏል ነው ያሉት።
በፀጥታ ችግር ምክንያት ሰነድ ማጓጓዝ ፈታኝ ከመኾኑ አኳያም የኦንላይን ኩነቶች ምዝገባ የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል። አንድን ሰነድ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ተቋም ለማጓጓዝ የሚወስደውን የተራዘመ ጊዜ እና የመጓጓዣ ወጭ ማስቀረት እንደተቻለም ገልጸዋል።
የኦንላይን ምዝገባውን በወልድያ ከተማ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ለምዝገባ ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!